የተገልጋዮችን ዕርካታ ለማረጋገጥ ብቁ ሙያተኞችን በብዛትና በጥራት ማፍራት አለብን - ጤና ሚኒስቴር

111

አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 በጤና ዘርፍ የተገልጋዮችን ዕርካታ ለማረጋገጥ ብቁ ሙያተኞችን በብዛትና በጥራት ማፍራት እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በማህፀንና ፅንስ፣ በውስጥ ደዌ፣ በቀዶ ህክምና፣ በጠቅላላ ህክምናና በህፃናት ህክምና፣ በማይክሮ ባይሎጂ በስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ በስነ ምግብና በህብረተሰብ ጤና በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ 169 ተማሪዎችን አሰልጥኖ አስመርቋል።

በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የጤና ባለሙያዎችን በጥራትና በብዛት ማሰልጠን እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በጤና ዘርፍ የባለሙያዎች እጥረት መኖሩን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በአሁኑ ወቅት 10 አዋላጅ ነርሶች ለ10 ሺህ እናቶች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አንስተዋል።

ለ10 ሺህ እናቶች 46 አዋላጅ ነርሶች መመደብ እንዳለባቸው ገልጸው፤ በጤና ተቋማት ተመድበው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ አዋላጅ ነርሶች ቁጥር ከሚጠበቀው በታች መሆኑን አመልክተዋል።

በጤና ተቋም የሚታየውን የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ሰልጣኞች ሙያዊ ስነ ምግባሩን ጠብቀው ሃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር በቀለ መንግሥቱ ተመራቂ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን ተጠቅመው የህብረተሰቡን የጤና ችግር በመቅረፍ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

በዕውቀት፣ ክህሎት፣ አመለካከትና ተግባር ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን ማፍራት፣ በቂ የህክምና ቁሳቁስና ፈጣን አገልግሎት መስጠት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በጤና ተቋማት ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሱና በስነ ምግባር የታነፁ ሙያተኞችን ለማፍራት ኮሌጁ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የሆስፒታሉ ዲን ዶክተር በቃና ለሜሳ እንደገለፁት፤ ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ባለፈ ኤም አር አይ፣ ሲቲ ስካን፣ ስፔሻሊስትና ሰብ ስፔሻሊስት ህክምና እየሰጠ ነው።

የሆስፒታሉን አገልግሎት ወደ ተሪሸሪ የምርምር ተቋም ለማሳደግ እየሰራን ነው ብለዋል።

በ18 የጤና ፕሮግራሞች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ፣ በሶስተኛ ዲግሪን ጨምሮ በስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ እያሰለጠነ ይገኛል ነው ያሉት።

ኮሌጁ ለደቡብ ሱዳንና ለሶማሊላንድ ተማሪዎች የትምህርት ዕድል በመስጠት እያስተማረ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም