በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በማጋለጥ ተጎጂዎች ተገቢውን ፍትሕና የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ ልምድ ሊዳብር ይገባል

389

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 ሕብረተሰቡ በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለሕግ አካል በመጠቆም ተጎጂዎች ተገቢውን ፍትሕና የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው ይህን ያስታወቀው “ምቹ እና ሰላማዊት ኢትዮጵያ ለሁሉም ህፃናት” በሚል በተከበረው የዓለም የህፃናት ቀን የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ላይ ነው።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሀና የሺንጉስ  እንደገለፁት፤ አብዛኛው ሕብረተሰብ በህፃናት ላይ ጥቃት ሲደርስ ለሕግ አካል የመጠቆም ልምድ የሌለው ሲሆን ዘግይቶ መረጃ በመስጠትም ብዙ ማስረጃዎች ይጠፋሉ።

በመሆኑም ሕብረተሰቡ  ህፃናት ላይ ጥቃት ሲደርስ በ72 ሰዓታት ውስጥ መጠቆም እንዳለበት ተናግረዋል።

ለዚህም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የጥቃት መጠቆሚያ የነፃ መስመር ስልክ 991 ሥራ ላይ መዋሉን ገልፀዋል።

የስልክ መስመሩ መኖር ለተጎጂዎች ነፃ የሕግ የምክር አገልግሎት ለመስጠት፣ የተጎጂዎችን የፍትሕ ሂደት ለመከታተልና የሕክምና እና ሥነ-ልቦና ምክር ለመስጠትም እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች መልካቸውን በየጊዜው እየቀያየሩ የሚፈፀሙ በመሆኑ ተመጣጣኝ ቅጣቶች መቀመጥ እንዳለባቸውም አክለዋል።

“የህፃናትን ጥቃት ለማስቆም ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል” ያሉት ኃላፊዋ ለዚህም በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልፀዋል።

ከእነዚህም ውስጥ “ኑ! ቡና እንጠጣ የሴቶችና ህፃናትን ጉዳይ እናውጋ” በሚል መሪ ቃል በከተማው የተደረገው ዝግጅት አንዱ ማሳያ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም 1 ሺህ 200 የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴዎች በማዋቀርና በማሰልጠን ወደ ሥራ እንደተገባም ገልፀዋል።

ሆኖም ይህ በቂ ባለመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ መገናኛ ብዙኃንና ሕብረተሰቡ የህፃናትን ጥቃት ለማስቆም በትብብር መሥራት አለባቸው ብለዋል።

የዓለም የህፃናት ቀን በዓለም ለ33ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።