ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከመንግሥት ጥረት ባለፈ የሁሉም ድጋፍና እገዛ መኖር አለበት

127

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከመንግሥት ጥረት ባለፈ ሁሉም የበኩሉን እገዛ ሊያደረግ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ተናገሩ።

12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ የአካል ጉዳተኞችና መስማት የተሳናቸው የስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል በይፋ ተከፍቷል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ፤ ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአሥር ዓመት መሪ እቅዱ አካቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአካል ጉዳተኞች የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎ በመንግሥት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው መከበርና ለደኅንነታቸው መጠበቅም እንዲሁ።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አብርሃም ታደሰ፤ የስፖርት ውድድርና ፌስቲቫሉ ዋነኛ ዓላማ አካል ጉዳተኞች በየትኛውም የሥራ መስክ መሰማራትና ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል።

ከዳኝነት ጀምሮ ሌሎችም ሥራዎች በአካል ጉዳተኞች እየተመሩ የሚከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በውድድሩ ምርጥ ስፖርተኞችን የማግኘት ዓላማም አለው ብለዋል።

የአዲስ አበባ አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ገለታው ሙሉ፤ አካል ጉዳተኞችን በሁሉም መስክ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግሥትም በኩል የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን አድንቀዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ከመንግሥት በተጨማሪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሌሎችም ጥረት ሊታከልበት ይገባል ነው ያሉት።

የተጀመረው የአካል ጉዳተኞች የስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል ለሰባት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ስፖርተኞች በሰባት የተለያዩ የስፖርት አይነቶች የሚወዳደሩ ይሆናል።

የዓለም የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ ሲከበር በኢትዮጵያ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ ኅዳር 24 ቀን 2015 ዓ.ም በድሬደዋ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም