የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ተጀመረ

109
አዲስ አበባ መስከረም 17/2011 የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ ምክር ቤት አዳራሽ ተጀምሯል። ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣይ አራት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው ጉባኤ "የለውጡ ቀጣይነት ለአማራ ህዝቦች ተጠቃሚነትና ዲሞክራሲያዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል። በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የንቅናቄው ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ   ከሁለት ሺህ 100 በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል። በጉባኤው ላይ 1 ሺህ 200  አባላት በድምጽ እንዲሁም 300 ደግሞ በታዛቢነት ይሳተፋሉ ተብሏል። በአራት ቀናት የድርጅቱ ጉባኤ የድርጅቱ አርማ እና ስያሜ ለውጥ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። ብአዴን የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀ መንበር ጨምሮ ሌሎች ዘመኑ የሚጠይቀውን ፖለቲካዊ አመራር መስጠትና የክልሉን ህዝብ ጥያቄ መመለስ የሚችሉ አካላትን ይመርጣል። ጉባኤው አሁን ብአዴን በሚከተለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ላይ ተወያይቶ ማሻሻያ ያደርጋል፤  በክልሉ ህዝቦች ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት፣ ከክልሉ ውጭ ያሉ የብሄሩ ተወላጆች እንዲሁም የክልሉን ወሰን በተመለከተ ፖለቲካዊ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም