በትግራይ ክልል በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

173

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 17 ቀን 2015 በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በክልሉ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች ጥገና ተደርጎላቸው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በመንግስትና ህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ያለ ገደብ እየቀረበ ይገኛል፡፡

በትግራይ ክልል ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ጨምሮ መድሃኒትና የህክምና መሳሪያ ለሚያቀርቡ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች መንግስት የሰብዓዊ ድጋፍ ማጓጓዣ ኮሪደሮችን ክፍት ማድረጉን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ በክልሉ በተለይ በጦርነቱ ሳቢያ ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡

በሚኒስቴሩ የአስቸኳይ ጊዜ መጠጥ ውሃና ልዩ ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ አቶ አስቻለው ተስፋዬ በሽሬ ከተማ በሰከንድ 48 ሊትር የተጣራ ውሃ መልቀቅ የሚችል የውሃ ማጣሪያ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የመጠገን ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ከሽራሮ እስከ አድዋ ባሉ አከባቢዎች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች የውሃ እጥረት እንዳያጋጥም ተጨማሪ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በመጠለያ ጣቢያዎች ከድጋፍ ሰጪ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ውሃ በቦቴ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በመጠለያ ጣቢያዎች የነበረውን የውሀ እጥረት መፍታት ተችሏል ብለዋል።

በትግራይ ክልል ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ለማሻሻል የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም