ህጻናትን ከጎዳና ህይወት ለመታደግ በጥናት የተደገፈ ሥራ እየሰራ መሆኑን ደቡብ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ገለጸ

120
ሀዋሳ መስከረም 17/2011 ህጻናትን ከጎዳና ህይወት ለመታደግ በጥናት ላይ የተደገፈ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የደቡብ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ገለጸ፡፡ ቢሮው የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ በሃዋሳ ከተማ በጎዳና ለሚኖሩ ህጻናት የምሳ ግብዣና የምክክር መድረክ አድርጓል፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የህጻናት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ባቲሪያ ቦረዳ እንደገለጹት ህጻናትን ከጎዳና ሕይወት ለመታደግ የችግሩን ምንጭ በጥናት ከመለየት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል የጎዳና ህጻናትን መረጃ የማደረጃት፣ ቤተሰባቸውን የማፈላለግና የማገናኘት እንዲሁም ለህጻናቱ ጎዳና መውጣት መሰረታዊ የሆኑ ምክንያቶችን የመለየት ሥራ ይጠቀሳሉ፡፡ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛና ህገ ወጥ ዝውውርን በመከላከል በኩል ተግዳሮቶች መኖራቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ባቲሪያ ባለፈው ዓመት በተሰራው ሥራ ከ1 ሺህ 300 በላይ የጎዳና ህጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ እንደኃላፊዋ ገለጻ ህጻናቱ በአብዛኛው በትምህርት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ወደትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ከቤተሰብና ከአካባቢ አመራር ጋር በመነጋገር የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ባለፈው ክረምት ወራት ቤተሰባቸውን ያገኙ በመሆናቸው በተያዘው የትምህርት ዘመን ወደትምህርት ገበታቸውና እንደሚገቡና ለእዚህም እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንጻር አሁንም በጎዳና ላይ ህጻናት መኖራቸውን ጠቀሰው በእንደዚህ ዓይነት በዓላት ለህጻናቱን የምገባ መርሀ ግብር ማዘጋጀት መሰረታዊ ችግራቸውን ለማወቅ እንደሚረዳ ነው የጠቆሙት፡፡ የመስቀል በዓል በክልሉ በድምቀት የሚከበር በመሆኑ ህጻናቱ ወገን እንዳላቸው እንዲረዱና ወደፊት ተስፋ የሰነቁ እንዲሆኑ ለማስቻል ውይይት ይደረጋል ብለዋል፡፡ ከህጻናቱ የሚገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ ሥራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በምሳ ግብዣው ላይ ከተሳተፉ የጎዳና ህጻናት መካከል ከለኩ ከተማ የመጣው ተረፈ በቀለ እናትና አባቱ በህይወት ባለመኖራቸው ወደ ጎዳና ህይወት መውጣቱን ተናግሯል፡፡ በጎዳና ህይወት ለምግብ እጥረት፣ ለልብስና መኝታ ችግር ከመጋለጡ ባለፈ በተለያዩ ጉልበተኞች ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተናግሯል፤ የመማር እድሉን ቢያገኝ ከጎዳና የመውጣት ፍላጎት እንዳለውም ነው የገለጸው፡፡ የደቡብ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ የመስቀልን በዓል ምክንያት በማድረግ የምሳ ግብዣና የውይይት መድረክ በማዘጋጀቱ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሌላኛው ህጻን መላኩ ሙሴ "የጎዳና ህይወት ለተለያዩ ሱሶች ስለሚያጋልጥ ሕይወቴ እንዲቀየር እፈልጋለሁ" ብሏል ፡፡ በተደረገላቸው ግብዣ ደስተኛ መሆኑንና እሱም ከዚህ ሕይወት ሲወጣ ተመሳሳይ ተግባር እንደሚፈጽም ተናግሯል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም