ክልሉ በአስቸኳይ የሙስና መከላከል እንቅስቃሴ ውጤት እያመጣ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታወቀ

150

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 16 ቀን 2015 የደቡብ ክልል በአስቸኳይ የሙስና መከላከል እንቅስቃሴ ውጤት እያመጣ መሆኑን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

በቅርቡ የተቋቋመው የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ የሙስና መከላከል ጥረቱ ላይ እያጋጠሙ ያሉ እንቅፋቶችን እንደሚያስወግድና የተጀመረውን የሙስና መከላከል ተግባር ውጤታማ ለማድረግ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተገልጿል።

በኮሚሽኑ የሙስናና ብልሹ አሰራር መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ፋሲካ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በአስቸኳይ የሙስና መከላከል እንቅስቃሴው ባለፈው በጀት ዓመት ከ378 ሚሊዮን ብር በላይ እና ከ38 ሺህ 900 በላይ ካሬ ሜትር የከተማና ገጠር መሬት በማስመለስ ሀብትን ከብክነት ማዳን መቻሉም አመልክተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በተመሳሳይ ምዝበራን የመከላከል ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ለሀብት ምዝገባ ትኩረት በመስጠት በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ሰራተኞች፣ አመራሮችና የህዝብ ተመራጮች ሀብት እንዲያስመዘግቡ መደረጉን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በሚያቀርበው አስቸኳይ የሙስና መከላከል ጥቆማና ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት በተደረገው ሰፊ ጥናትና በተሰጠው ግብረ-መልስ ውጤታማ ስራ መከናወኑን አውስተዋል።

ኮሚሽኑ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል የውሳኔ ተፈጻሚነት ላይ ያለውን ችግር በዋናነት አንስተዋል።

በየደረጃው ያሉ አካላት ተወስኖ ተፈጻሚ እንዲሆን የተላኩ ጉዳዮችን ሳይፈጽሙ ፈጽመናል ማለትን ጨምሮ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ አለመፈጸም ክፍተቶች እንዳሉባቸው ጠቁመዋል።

ይህም የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ በማሰናከል የተገልጋዮች እርካታን እንደሚቀንስ ገልጸው፤ ድርጊቱና ጥፋቱ በህግ እንደሚያስጠይቅ አመልክተዋል።

ከውሳኔ ተፈጻሚነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ግድፈቶችን የሚመለከታቸው አካላት በአፋጣኝ እንዲያርሙ ምክትል ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

በመሆኑም እንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት በሀገር ደረጃ ችግሩ የሚፈታበትን ስልት በመንደፍ የተለየ ግብረ-ኃይል ማቋቋም ተገቢነት እንዳለው አመላክተዋል።

በቅርቡ የተቋቋመው የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ የሙስና መከላከል ጥረቱ ላይ እያጋጠሙ ያሉ እንቅፋቶችን እንደሚያስወግድና የተጀመረውን የሙስና መከላከል ተግባር ውጤታማ ለማድረግ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ህዳር 08 ቀን 2015 ዓ.ም መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም