የአማራ ክልል የጤና መረጃ ለማደራጀትና ደህንነቱን ለማስጠበቅ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

125

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 16 ቀን 2015 በአማራ ክልል የጤና መረጃን በዘላቂነት ለማደራጀትና ደህንነቱን ማስጠበቅ የሚያስችል የአንድ ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና በካናዳው "ማኒቶባ ዩኒቨርሲቲ" ትብብር ለሦስት ዓመት የሚተገበር መሆኑም ተገልጿል።

የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በክልሉ የተጠናከረ የጤናው ዘርፍ መረጃ አያያዝ ስርዓት እንዲኖር የሚያደርግ ነው።

ቀደም ሲል በዘርፉ የበቃ ባለሙያ፣ ቴክኖሎጂ እንዲሁም የፋይናንስ እጥረት የተነሳ የጤና የመረጃ አያያዙን በሚጠበቀው ልክ ማከናወን እንዳልተቻለም አንስተዋል።

በዚህም የጤና መረጃን ከላይ እስከታች ባሉ የጤና ተቋማት ወጥ በሆነ መንገድ ተደራጅቶ ተደራሽ በማድረጉ ረገድ ክፍተቶች እንደነበሩም አክለዋል።

ይህ ፕሮጀክት የክልሉን የጤና መረጃ አያያዝ በማሻሻል፣ በመተንተንና በአግባቡ በመሰነድ እንደየ ሁኔታው ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችልና ለውሳኔ ሰጭ አካላት የተሟላ መረጃ እንዲደርስ የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚቀመረው መረጃም ለፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ግብዓት በማድረግ፣ ዘርፉን ለመከታተልና ተገቢ የሆኑ ውሳኔዎችን ለመወሰን ያስችላል ብለዋል።

በ"ማኒቶባ ዩኒቨርሲቲ" ዓለም አቀፍ የህዝብ ጤና ተቋማት ረዳት ፕሮፌሰር ደሳለኝ መለሰ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓት የተሻለ እንዲሆን የአቅም ማጎልበቻ ስራ የሚሰራ ነው ብለዋል።

ዛሬ ከአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ይፋ የተደረገው ‘’ዳሱ’’ (Data Analysis System Use) ፕሮጀክት 1 ሚሊዮን ዶላር የተመደበለት ሲሆን ለቀጣይ ሦስት አመታት የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ለማዘመን የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ባለሙያዎችን ቀጥሮ ወደ ስራ መግባት መቻሉን ገልጸው፤ ለውጤታማነቱ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ከክልሉ የሚገኘውን ልምድ በመቀመርም ፕሮጀክቱ በቀጣይ በሃገር አቀፍ ደረጃ በሌሎች ክልሎች እንደሚሰፋም አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱ በባህር ዳር ከተማ ይፋ ሲደረግ የአማራ ክልል የጤናው ዘርፍ አመራሮች፣ የ"ማኒቶባ ዩኒቨርሲቲ" ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም