የፌዴራል ፖሊስ ተቋማዊ አቅሙን በማጎልበት የህዝብን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር ድንበር ታሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከል ላይ በትኩረት እየሰራ ነው

201

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 16 / 2015 የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ተቋማዊ አቅሙን በማጎልበት የህዝብን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር ድንበር ታሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፋንታ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ አደረጃጀትን ዓለም አቀፋዊ የፖሊስ ዶክትሪን መሰረት ባደረገ መልኩ የማዘመንና የላቀ ህዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል።

በሰራዊት አባላት ውስጥ የአፈጻጸም ግድፈቶች እንዳይኖሩ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ የአፈጻጸም ጥሰትን በፍጥነት ማረም የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል ነው ያሉት፡፡

ይህም የፌደራል ፖሊስ አሰራርን በማዘመንና ተልዕኮውን በብቃት እንዲፈጽም በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን የልማት ግስጋሴ ለመግታት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጸረ-ሰላም ኃይሎችን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና መወጣቱን ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ መሰረተ ልማቶች እንዳይስተጓጎሉ ህዝብ የጣለበትን ኃላፊነት መወጣቱንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የፀጥታ ስጋት በነበረባቸው አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን መደረጉን ገልፀው፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከልና ካማሽ ዞኖች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሳቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በተጨማሪም ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ፣ የአቪየሽን ፖሊስ፣ የዩኒቨርሲቲ ፖሊስ፣ የምድር ባቡር፣ የአድማ ብተና፣ የድንበርና ፀረ ኮንትሮባንድ፣ የፖሊስ ኮማንዶ እና ሌሎች አደረጃጀትችን በመምሪያ ደረጃ በማዋቀር የወንጀል መከላከል አቅሙን ማሳደጉን ተናግረዋል።

ከዚህ የአወቃቀርና አደረጃጀት ማሻሻያዎች ባሻገርም የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ ግብዓቶች በማሟላት የአገርና የህዝብ ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በተሻለ አፈጻጸም እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በጎረቤት አገራት የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀትና የጋራ ዕቅድ በማውጣት ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን የመከላከያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

በዚህም በተለይ በርካታ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርቶችን እና የማዕድን ውጤቶችን በኮንትሮባንድ ንግድ ከአገር የማስወጣት እና አደንዛዥ ዕፅና የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶችን ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ አመርቂ ውጤት መመዝገቡንም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በአፍሪካ ደረጃ ስመ-ጥር የፖሊስ ተቋም የመሆን ግብ ሰንቆ ተቋሙን ለማዘመን የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ አንደሚቀጥልም ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም