የአገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎችን መለየትንና አጀንዳ ማሰባሰብን ያለመ ምክክር በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው

101

ጅማ (ኢዜአ) ህዳር 16 ቀን 2015 የአገራዊ ምክክር ተሳታፊዎችን መለየትንና አጀንዳ ማሰባሰብ ላይ ያለመ ምክክር በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተሳታፊዎችን መለያና አጀንዳን ማሰባሰብ አስመልክቶ በጅማ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ ከጂማ ዞን፣ ከቡኖ በደሌና ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የተውጣጡ የሕብረተሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በውይይቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም የምክክር ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት በግልፅ ውይይት ለመፍታት የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ብዙ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች መሆኑን ጠቅሰው እነዚህን ፈተናዎችና ችግሮች ለማለፍም አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በግልጽ ከላመነጋገርና ካለመወያየት ለሚስተዋሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄው እንደ አገር ተቀራርቦ በግልፅ መነጋገርና መመካከር እንደሆነም ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህንን አካታችና አሳታፊ አገራዊ ምክክር እንደ እድል በመጠቀም ሊነሱ የሚገባቸውን አጀንዳዎች እና መሳተፍ ያለባቸውን ግለሰቦችን ጭምር በተመለከተ ሰፊ ውይይት ይደረጋል ብለዋል።

በጅማ ከተማ ዛሬ የተጀመረው ውይይት የዚሁ አካል መሆኑንና መሰል ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በየአካባቢያቸው ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ያሉ ችግሮችን ያነሳሉ፣ መመረጥ ስላለባቸው ተሳታፊዎች ሀሳብ ይሰጣሉም ብለዋል።

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃን ናስር በበኩላቸው ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተልዕኮ ስኬት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

ለአገራዊ ምክክር መድረኩ ስኬታማነት የሁሉንም ቀና ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም