”የደመራን በዓል ስናከብር የተቸገሩ ወገኖቻችን በመርዳትና አንድነታችንን በማጎልበት ሊሆን ይገባል”-አቡነ-ቀሌምንጦስ

578

ደብረብርሀን/ባህር ዳር መስከረም 17/2011 የደመራን ብዓል ስናከብር የተቸገሩ ወገኖቻችን በመረዳትና አንድነታችንን በማጎልበት ሊሆን ይገባል ሲሉ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ-ቀሌምንጦስ ተናገሩ።

የመስቀል ደመራ በዓል በደብረብርሃን ከተማ ዘርዓ ያዕቆብ ስታዲዬም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

ብፁዕ አቡነ-ቀሌምንጦስ ትናንት ማምሻውን በከተማው የደመራ በዓል ሲከበር እንዳስገነዘቡት በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳት መሆን አለበት፡፡

በዓሉን ከሌሎች ሃይማኖቶችና ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመረዳዳት አባቶቻችን ያቆዩንን ድንቅ ባህል ሳንበርዝና ሳንከልስ በጋራ ማክበር አለብን ብለዋል።

በዚህም ጥንታዊ ባህሉን፣ወጉንና ታሪኩን  ጠብቆና ሳይሸራረፍ እንዲከበርም አሳስበዋል።

በዓሉን በፍቅርና በአንድነት ማክበር የቻልነዉ ሰላም በመኖሩ ነዉና ወጣቱና ኅብረተሰቡ የአካባቢዉን ሰላም ነቅቶ በመጠበቅ ለዉጡ እንዳይደናቀፍ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ንጉሡ ወርቁ በበኩላቸዉ መንግሥት ታሪካዊ በዓሎች ሳይበረዙና ታሪካቸዉን ሳይቀየሩ በማክበር ለቀጣዩ ትዉልድ ለማስተላለፍ የዕቅድ አካል አድርጎ በመሥራት ላይ ይገኛልብለዋል፡፡

በማንኛዉም ጊዜ ማንነታቸዉ ያልታወቁና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ለጸጥታ ኃይሉ በመጠቆም ኅብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ተወካዩ አሳስበዋል፡፡

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ወልደጻዲቅ መላኩ የመስቀል  በዓልን የአካባቢያቸዉን ሰላም በመጠበቅና  ያላቸውን ለሌሎች በማካፈል ለማክበር መዘጋጀታቸዉን ገልጸዋል፡፡

የበዓሉን ታሪካዊነት ጠብቀዉ ለትዉልድ ለማስተላለፍም የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ “መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ የጥልን ግድግዳ ያፈረሰበትና የፍቅርን ሃያልነት ያሳየበት በመሆኑ ክርስቲያኖች ለሰው ልጅ ሁሉ ፍቅርን በእኩልነት ልትቸሩት ይገባል”ሲሉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሃም ገለጹ።

የደመራ በዓል በባህር ዳር ከተማ የሃይማኖት አባቶች፣የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

አቡነ አብርሃም በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት አባታዊ ምክር እንደገለጹት መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ የጥልን ግድግዳ ያፈረሰበትና ለፍቅር ሲል  እስከሞት ድረስ ራሱን አሳልፎ የሰጠበት ነው።ይህንንም ያደረገው  ለአዳምና ሄዋን ልጆች ሁሉ መሆኑን አስተምረዋል።

“ስለሆነም ክርስቲያኖች የመስቀል በዓልን ስታከብሩ  በሆይ ሆይታ ሳይሆን ምስጢሩን ተረድታችሁ ለሰው ልጆች ሁሉ የተከፈለ ዋጋ ስለሆነ ሰው የተባለን ፍጡር እኩል ልታዩት ይገባል” ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ባልተለመደ ሁኔታ ዘረኝነት የሚባል ወረርሽኝ ገብቷል ያሉት አቡነ አብርሃም፣ይህ ሃይማኖት፣ብሄርና ዘርን መሰረት ያደረገው ፍቅር ለመስቀል የተከፈለውን የፍቅር ዋጋን የዘነጋና ከግል ስሜት እንደሚመነጭ አስረድተዋል።

መስቀል በአንገታቸው አስረው ፍቅርን በመለገስ ፈንታ ጥላቻና ዘረኝነትን ፣በመተባበር ፈንታ መለያየትን፣በማቀፍ ፈንታ ማግለልን የሚሰብኩትን ቤቴክርስቲያኒቱ በጽኑ ታወግዛቸዋለች ሲሉም ተናግረዋል።

ዘረኝነት እንዲጠፋና ፍቅር እንዲነግስ ተግቶ መፀለይ እንደሚያስፈልግ የመከሩት አቡነ አብርሃም፣ ጥላቻና ዘረኝነትን የሚሰብኩ ወገኖችን መምከርና መገሰጽ እምቢ ካሉም የእኩይ ተግባራቸው ተባባሪ ላለመሆን የሰይጣን ተግባር ተባባሪነታቸውን በግልጽ ማሳየት ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም በዓሉን የተራቡትን በማብላት፣የታመሙትን በመጠየቅ፣የታረዙትን በማልበስ ማክበር እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየው በበኩላቸው የዘንድሮ የመስቀል በዓል አንድ ሁነው እንደ ሁለት ሲተዳደሩ የነበሩት ሲኖዶሶች አንድ በሆኑበት ወቅት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያኗ ግብረ-ገብነትንና ኢትዮጵያዊ ስነ-ምግባርን በማስተማር ታሪክ የማይረሳው የውለታ ባለቤት መሆኗን ገልጸው፣ለአገራዊ አንድነትም መጠናከር አስተዋጽኦዋን ማድረጓን እንድትቀጥልም ጠይቀዋል።

የዘንድሮው በዓል አገራዊ አንድነት፣ፍቅርና መቻቻል እየተሰበከበት ባለበት ወቅትና በሃሳብ ልዩነት ምክንያት በውጭ ሲኖሩ የነበሩ በነጻነት ወደ አገራቸው ገብተው በማክበራቸው ልዩ ያደርገዋል ያሉት ደግሞ የበዓሉ ታዳሚ አቶ ጌትነት ይበልጣል ናቸው።

በዓሉ ፍቅርና  አንድነት እየተሰበከበት ባለበት ወቅት መከበሩ የተለየ እንደሚያደርገው የገለጹት ወይዘሮ ቢተውሽ አሻግሬ ናቸው።