የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እና የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

159

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 15 ቀን 2015 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስርዓትን ለማጠናከር የሚረዳ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።

የስምምነቱ ዓላማ ሁለቱ ተቋማት የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙኃን አሰራር ለማዘመንና ለማሳደግ እንዲሁም የእርሰ በእርስ ቁጥጥር ስርዓትን ማጠናከርና ተግባራዊ ማድረግን በተመለከተ በትብብር ለመስራት ነው።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን በመፍጠር ከሙያው ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችንና ማንዋሎችን በትብብር ለማዘጋጀት ያግዛል ብለዋል።

በሀገሪቱ የሚዲያ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሙያዊ ስነ-ምግባር የተላበሱ፣ ብቁና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል እንዲሁም ከህዝብና ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና መረጃዎችን በመለዋወጥ የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስርዓቱ እንዲጠናከር ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስርዓቱን በማጠናከር የመገናኛ ብዙኃን ዘርፉን ለማሳደግ ሁለቱም በመደጋገፍ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

በስምምነቱ ወቅት የምክር ቤቱ አባል የሆኑ መገናኛ ብዙሃንን በሚመለከት ለባለሥልጣኑ የሚቀርቡ ጥቆማዎች እና ቅሬታዎች በምክር ቤቱ በኩል ሙያዊ ውሳኔ እንዲያገኙ የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚመቻችም መገለጹን ከባለ ሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከ60 በላይ የመገናኛ ብዙኃንና የሙያ ማህበራትን ያቀፈ ተቋም መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም