ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት ሲቀባበል የኖረ ባህላዊ ትውፊት በመሆኑ ትውልዱም በአግባቡ ማስቀጠል ይጠበቅበታል - ምሁር

297
አዲስ አበባ መስከረም 17/2011 የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ ለዘመናት ሲያከብረው የኖረ በመሆኑ ትውልዱም እሴቱን ሳይለቅ ማስቀጠል እንደሚገባ አንድ ምሁር ተናገሩ። የባህልና ታሪክ ተመራማሪ አቶ ድሪቢ ደምሴ  ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ "ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ በወቅቱ ዘንቦ በወቅቱ አባርቶ ምድር እንድትለመልም፣ እህል እንዲያፈራና ህይወት እንድትቀጥል ያደረገው ፈጣሪን የሚያመሰግንበት በዓል ነው" ብለዋል። ይህ በዓል "ባህላዊም ሃይማኖታዊም ይዘት አለው" የሚሉት ተመራማሪው ይህ ስርዓት ለረዥም ጊዜ ሲከወን መኖሩን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ ብለዋል። በዓመት ሁለት ዓይነት ኢሬቻዎች የሚከበሩ ሲሆን አንደኛው የበጋ ወራት አልፎ በልግ ሲመጣ የሚከበርና ተራራ ላይ ተወጥቶ ፈጣሪ የሚለመንበት 'ኢሬቻ ቱሉ' በማለት የሚታወቅ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የክረምት ወራት ተገባደው የበጋ ወራት መጀመሪያ አካባቢ ወንዝ ላይ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ''ኢሬቻ መልካ'' በመባል የሚታወቅ ነው ሲሉ አብራርተዋል። የ'ኢሬቻ ቱሉ' በዓል የሚከበርበት ምክንያት በጋው በወቅቱ አልፎ ዝናብ መሬት እንዲያለመልም ፈጣሪን ለመለመንና ክረምቱን በሰላም እንዲያሻግር ልመና የሚከናወንበት መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ ቀንም ሲከበር "የራሱ የሆነ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ  ባህላዊ ስርዓት አለው" የሚሉት ምሁሩ፤ ኦሮሞ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ''ሰባ ስንብራ ቁብስ'' እያለ ምድር ላይ ላለው ፍጥረት ሁሉ የተድላ ህይወት እንዲኖር የሚጸልይበት ቀን ነው ይላሉ። በስፍራው ሲካሄድም በባህሉ የተለመደው ሰው ሁሉ የክት ልብሱን ለብሶ በጋራ ሆኖ ባህላዊ ዜማ እያዜሙ መደሰት ነው ያሉት አቶ ድሪቢ የኢሬፈና ስንስርዓት የሚከወንበት ቦታ ላይ ፉከራ ቀረርቶና ለጦርነት የሚያነሳሱ ዜማዎች የተከለከሉ ናቸው ብለዋል። የጦር መሳሪያም ይዞ ወደ ስፍራው መሄድ እንዲሁ የተከለከለ መሆኑን በመግለጽ ወጣቱም ትውልድ ከተከለከሉ ድርጊቶች በመቆጠብና አከባበሩን ከአባቶች በመማር ቱባ ባህሉ ሳይበከል ማስቀጠል ይገባዋልም ብለዋል። በዓሉ አሁን አሁን የሌሎችንም ብሄሮችና የውጭ ዜጎችን ቀልብ እየሳበ በመሆኑ አገር የማስተዋወቅና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙም እየጎላ መምጣቱን የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ይህ በአግባቡ ተይዞ ወደ ሃብትነት መቀየር አለበት ሲሉም መክረዋል። በየዓመቱ የመስቀል በዓል አልፎ ባለው እሁድ ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል፤ የዘንድሮው እሁድ መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚከበር ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም