የመስቀል በዓልን አብሮነትን በሚያጠናክርና በፍቅር ማክበር ይገባል

59
ድሬዳዋ መስከረም 17/2011 የመስቀል በዓልን አብሮነትን በሚያጠናክርና በፍቅር ማክበር እንደሚገባ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ሰብከት ሊቀጳጳስ ብፁህ አቡነ ሩፋኤል ገለጹ። የደመራ በዓል በጋምቤላና በድሬደዋ ከተሞች በድምቀት ተከብሯል። በጋምቤላ ከተማ ትናንት በተከበረው የደመራ በዓል ላይ ብፁነታቸው ተገኝተው ለምዕመናኑ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት የመስቀል በዓል የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት ነው። በመሆኑም ህዝበ ክርስቲያን የመስቀል ደመራ በዓልን ሲያከብር እርስ በእርስ በመዋደድ፣ አብሮነቱን በማጠናከርና በፍቅር ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል። በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዓመታት በዜጎች መካከል የነበረውን የአንድነትና የአብሮነት እሴትን በማጠናከርና አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት የተጀመረውን የልማት ጎዞ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል። በተለይም ወጣቱ ከጥላቻ ይልቅ በመዋደድ ማንኛውንም ጥያቄ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማቅረብና በመነጋገር ችግሩን ሊፈታ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። አንዳንድ የበዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በጋራ መፍታት የሚቻለው ሰላም ሲኖር መሆኑን ጠቁመው በክልሉ ሰሞኑን ደፍርሶ የነበረውን ሰላም ለማስመለስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል። በተመሳሳይ የመስቀል ደመራ በዓል በብዙ ሺህ የሚገመቱ የክርስትና እምነት ተከታዮች በተገኙበት በድሬዳዋ ከተማ በድምቀት ተከብሯል። ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያን በተውጣጡ መዘምራን ዝማሬዎች ደምቆ በተከበረው የደመራ በዓል ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ቁጥራቸው በብዙ ሺህ የሚገመት የክርስትና እምነት ተከታዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ማቲያስ በቀለ በበዓሉ ላይ እንዳሉት ቤተክርስቲያኗ አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍንና እንዲጎለብት አብዝታ ትስራለች ብለዋል፡፡ በሀገርና በሰው ላይ ክፉ የሚያስቡት ወደ ፍቅር፣ ወደ ሰላምና ወደ አንድነት እንዲመለሱ ሌት ተቀን የበኩሏን ጥረት እያደረገች መሆኗንም አመልክተዋል። በበዓሉ ሥነ ሥርዓት ላይ የተካፈሉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አብደላ አህመድ የእምነት ተቋማት አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር እያደረጉት ላለው ጥረት አመስግነዋል፡፡ በድሬዳዋም ሆነ በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን የእምነት ተቋማቱ እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ አመስግነው ይህን ተግባራቸውን በማጠናከር ሀገሪቱ የጀመረችውን የፍቅርና የመደመር ጉዞ ከዳር ለማድረስ በቀጣይም ተግተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ "ድሬዳዋ ብሔር ብሔረሰቦች፤ የተለያዩ እምነቶች በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት ከተማ ናት፤ ይህን ፍቅር፣ ህብረትና ሰላም ለመበጥበጥ ሌት ተቀን የሚጥሩ አካላት እኩይ ተግባራቸው አይሳካላቸውም ’’ ብለዋል፡፡ በበዓሉ የተሳተፉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህር ገብረክርስቶስ ገብረማርያም በበኩላቸው የመስቀል ደመራ በዓል የተጣላ የሚታረቅበት፤ የተራራቀ በፍቅር የሚገናኝበት መሆኑንና በዓሉን ሁሌም በእዚህ መልክ እንደሚያከብሩት ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው ወጣት ተማሪዎች በአንድነት፣ በፍቅርና በሰላም በመንቀሳቀስ ሀገራቸውን ወደተሻለ ደረጃ እንዲያደርሱ የሚሰጡትን ምክር እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል፡፡ ሌላዋ የበዓሉ ታዳሚ ወጣት ኤፍራታ ኃይሉ በበኩሏ ለአካባቢያቸው ሰላምና ፀጥታ መጠበቅ ወጣቱ ከፍትህ አካላት ጋር ተባብሮ መስራት እንዳለበት ነው የተናገረችው፡፡ የደመራ በዓል የተከበረበትን ቦታ በማዘጋጀት ሥራ ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጭምር ማገዛቸው ለዘመናት ያለንን አብሮነት ያሳያል ያለችው ደግሞ ዘማሪ አድና ሞገስ ናት። እንዲህ አይነቱን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ መሆኑን ቀጥላለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም