ባህር ዳር ከተማን በቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ነው

198

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 15 ቀን 2015 ባህር ዳር ከተማን በቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ የአካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አወቀ ፈንታ ለኢዜአ እንዳሉት ባህር ዳር ከተማ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ የበለጠ በማሳደግ የቱሪስት የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

በጣና ሃይቅ ዳርቻ የሚገኙ የህዝብ ፓርኮችን ደረጃ የማሳደግ፣ የመንገድ አካፋይና የእግረኛ መንገድ ዳር አካባቢዎችን የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ዲፖ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን 4 ሄክታር ስፋት ያለው መሬት በ86 ሚሊየን ብር የማልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በተጨማሪም 1 ነጥብ 8 ሄክተር ስፋት ያለውን ህዳር 11 የህዝብ ፓርክ ለሁለት ማህበራት በመስጠት ደረጃውን በጠበቀ አግባብ የማልማት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

ሹም አቦ፣ ጂንአድና ሌሎች የህዝብ ፓርኮችን ደረጃ በደረጃ ለማልማት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የጣና ሃይቅን ጨምሮ የተፈጥሮ ጸጋዎችን መሰረት በማድረግ እየተካሄዱ ያሉ የአረንጓዴ ልማት ስራ ለከተማው ህዝብ እና ለጎብኝዎች ምቹና ሳቢ የመዝናኛ ስፍራዎች እንደሚፈጥሩ አስታውቀዋል።

ሀላፊው አክለውም የህዝብ ፓርኮችን፣ የመንገድ አካፋዮችን፣ የእግረኛ መንገድ ዳርና ሌሎች አካባቢዎችን በአረንጓዴ ለማልማት 265 አባላት ያሏቸው 12 ማህበራት ውል ወስደው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ልማት የሚካሄድባቸው አካባቢዎች የውሃ መስመር እስከሚዘረጋላቸው ድረስ 11 ቦቴዎች በኪራይ ቀርበው ሳር፣ አበባና ሌሎች ተክሎችን ውሃ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

"የአረንጓዴ ልማት ስራው ለማህበራት ከተሰጠ ወዲህ አበረታች ለውጦች መጥቷል" ያሉት ሀላፊው የከተማ አስተዳደሩ ለአረንጓዴ ልማት ስራው  በየወሩ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጭ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በከተማው የሚገኙ አደባባዮች የከተማዋን ታሪክ፣ ጸጋና ባህል መሰረት ያደረጉ ሃውልቶች ለመሰራትና በአረንጓዴ ለማልማት የዲዛይን ስራ እየተከናወነ መሆኑን ሀላፊው አስታውቀዋል።

በአረንጓዴ ልማት ስራ የተሰማራው ማህበራቸው ለ80 ሰዎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል መፍጠሩን የገለፀው ደግሞ የሙሉቀን፣ መሰረትና ጓደኞቻቸው የገጸ ምድር ማስዋብ ማህበር ስራ አስኪያጅ ወጣት ሙሉቀን ይኑር ነው።

ከጣና ሃይቅ ጋር የተያያዘውን የህዳር 11 የህዝብ መናፈሻ ፓርክን በተሻለ ዲዛይን ለማልማት እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም