የአካባቢ ጥበቃ ሕግን ተግባራዊ ባላደረጉ 87 ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

139

አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 15/2015 የአካባቢ ጥበቃ ሕግን ተግባራዊ ባላደረጉ 87 አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ባካሄደው የክትትልና ቁጥጥር ግኝት ውጤት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየመከረ ይገኛል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ እንዳሉት በተደረገው የአካባቢ ህግ መከበር ክትትልና ቁጥጥር 72 የማምረቻ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል።

በተጨማሪም 15 የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደተወሰደባቸው አመልክተዋል።

በዚህም አስር ፋብሪካዎችን እስከ መዝጋትና ለተቀሩት ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያን ጨምሮ ሌሎች አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር በሕጉ አፈፃፀም ላይ ክፍተት የታየባቸው 47 የማምረቻ ተቋማት የተሰጣቸውን ግብረ መልስ ወስደው ክፍተቶቻቸውን ማረማቸውን ገልጸዋል።

በማሳያነትም የቆዳ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች፣ ብረታ ብረት፣ የአልኮልና ቢራ ፋብሪካዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ የተቀናጀ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና አወጋገድ ስርዓት ተግባራዊ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በተመሳሳይ የተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣ የአየር ብክለት መከላከያ ቴክኖሎጂን ጨምሮ የኬሚካል ማከማቻዎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ማድረጋቸውም ተገልጿል።

በመድረኩ የተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው እንዳሉት የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እየተደረገ ነው።

በማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በሃይቆችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዙሪያ የአካባቢ ጥበቃ ሕጉ ተግባራዊነት ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እያከናወነ ይገኛል ያሉት ኃላፊው በውሃ አካላት፣ በከባቢ አየር፣ በአፈርና በድምፅ ብክለት ደረጃዎች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልልና በፌዴራል ደረጃ ባለፈው ዓመት ከ14 ሺህ 500 በላይ አምራች ተቋማት፣ 3 ሺህ የልማት ፕሮጀክቶችና 5 ሺህ 927 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የአካባቢ ህግ መከበር ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የአካባቢ ተፅዕኖ አዋጭነት ጥናት መካሄዱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም