የደመራ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግርና የትራፊክ አደጋ በሰላም ተጠናቋል-አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

56
አዲስ አበባ መስከረም 17/2011 ትናንት በአዲስ አበባ የተከበረው የደመራ በዓል ያለምንም ፀጥታ ችግርና የትራፊክ አደጋ በሰላም መጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። በዓሉ በተሳካና በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ላደረገው አስተዋፅኦም ኮሚሽኑ ምስጋና አቅርቧል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበረው የመስቀል በዓል ትናንት በመዲናዋ አምብርት መስቀል አደባባይ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች፣ የውጭ አገር ጎበኚዎችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። በቤተክርስቲያኗ የከተማዋ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ሊቃውንት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ሌሎችም የበዓሉ ታዳሚዎች ናቸው። በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ተደርጎ አውቅና የተሰጠውና ዓለም አቀፍ ጥበቃ የሚደረግለት የደመራ በዓል በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ውጪ በመላ አገሪቷ በድምቀት ተከብሯል። የአዲስ አበባ ፖሊሰ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር ይጠናቀቅ ዘንድ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ የከተማው ነዋሪ በተለይም ወጣቱ በዓሉ በታላቀ ድምቀት ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ ያደረገው አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ኮማንደር ፋሲካ ገልፀዋል። የሰንበት ተማሪዎችና የበዓሉ ታዳሚ ምእመናንም ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን ያሳየው ትብብር የሚደነቅ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል። በአዲስ አበባ የፀጥታ ችግርና የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር መንገዶችን መዝጋት ጨምሮ ፖሊስ ያደረጋቸው በነበሩት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች  ህዝቡ ያሳየው ተባባሪነት ከፍተኛ እንደነበርም ተገልጿል። በዚህም በዓሉ ካለምንም ችግር ተከብሮ አልፏል ያሉት ኮማንደር ፋሲካ መላው ህብረተሰብ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል። አያይዘውም በዛሬው እለት በሚከበረው የመስቀል በዓል ላይ  የትራፊክ አደጋን ጨምሮ ሌሎች አላስፈላጊ ጉዳቶች እንዳይከሰቱ ህዝቡ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲዝናና አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም