በመርሀ ግብሩ በቀጣይ አራት ዓመታት ሁሉንም አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል- ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው

132

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 14/2015 በደቡብ ክልል በቀጣይ አራት ዓመታት በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ሁሉንም የክልሉን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች እንደሚከናወኑ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

የደቡብ ክልል የሌማት ትሩፋት ማስጀመሪያ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ  በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ተካሂዷል ።

በመድረኩ ላይ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት  በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በሚቀጥሉት አራት አመታት በእንስሳት እርባታ፣ በጓሮ አትክልት፣ ስራስርና እንሰት ልማት መላውን የክልሉን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ይከናወናሉ።

ክልሉ ለእንስሳት እርባታ፣ ለአትክልትና እንሰት ልማት ያለውን ዕምቅ ሀብትና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እንደሚሰራ ተናግረዋል ።

በተጨማሪም  በወተት፣ ስጋ፣ ዶሮና እንቁላል ላይ በማተኮር ሁሉንም አርሶ አደር በማሳተፍ እንደሚሰራ አመላክተዋል ።

በክልሉ የሚገኙ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል በወተት፣ በስጋና  በዶሮ አርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን እንዲያጎለብት እንደሚደረግ ገልጸዋል ።

ከአንስሳት እርባታ ጋር ተያይዞ የመኖ እጥረት እንዳያጋጥም በየአካባቢው የመኖ ልማት በትኩረት እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ልማቱን ለማጠናከር በሚደረገው ርብርብ የግብዓቶች እጥረትና የገበያ ክፍተት እንዳይፈጠር ከወዲሁ እንደሚሰራ ተናግረዋል ።

ለመርሀ ግብሩ ተግባራዊነት የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ሁነኛ መሳሪያዎች እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

መርሀ ግብሩ ስኬታማና ተሞክሮ የሚቀሰምበት እንዲሆን ሁሉም አመራር በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ርእሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ የእንስሳት ዝርያን ለማሻሻል በማድራትና ዘመናዊ ማዳቀል ዘዴን ጥቅም ላይ በማዋል ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም በርካታ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ጠቁመዋል።

ተሞክሮውን  በማስፋት በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ሁሉንም የክልሉን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች እንደሚሰሩ አመልክተዋል ።

በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች ያሉ ሀብቶችና ተሞክሮዎችን በመለየት የትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ልማቱ መገባቱን  አቶ ኡስማን  አስታውቀዋል ።

ለአንድ ቀን በተካሄደው መድረክ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ዋና አስተዳዳሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም