የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በመልካም ስብዕናና እውቀት የተገነባ ወጣት መፍጠር ይገባል -ሚኒስቴሩ

522

ጋምቤላ (ኢዜአ ) ህዳር 13/ 2015 የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በመልካም ስብዕናና እውቀት የተገነባ ወጣት መፍጠር እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስገነዘበ ።

‘‘የወጣቶች ንቁ ተሳትፎና ተካታችነት ለስብዕና ልማት’’ በሚል መሪ ሃሳብ 16ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ቀን ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በወቅቱ እንዳሉት  የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግና ራዕይዋን ማሳካት የሚቻለው ወጣቱን ትውልድ በመልካም ስብዕናና እውቀት ማነጽ ሲቻል ነው።

የሀገርን ሰላም፣ልማትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለማጽናትም ሁሉም የኢትዮጵያ ወጣት ዘብ ሊቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ወጣትነት በርካታ አካላዊ፣ አዕምሮና ስነልቦናዊ ለውጦች የሚገነቡትና ለቀጣይ ህይወት መሰረት የሚጣለበት ወርቃማ የእድሜ ክልል መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎች በእውቀትና መልካም ስነምግባር እንዲታነጹ የቤተሰብ ፣የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት ጨምሮ የሌሎች ባለድርሻ አካላት የላቀ ሃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ሚኒስትሯ አክለው ወጣቱ ትውልድ ለሱስና ለአልባሌ ስብዕና እንዲሁም ለህይወት መሰናክል እንዳይዳረግ ከሚደረገው የክትትልና የቁጥጥር ተግባር በተጨማሪ ለሀገር ልማት የሚወጡ ፖሊሲዎችን ከወጣቱ ስብዕና ልማት ጋር የማይጣረሱ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

እየጨመረ ከመጣው የወጣቶች ቁጥር አንፃር የስነ-ተዋልዶና ጤና አገልግሎትን በማስፋፋት ትውልዱን ከችግር በመታደግ ለአገር እድገት ማሰለፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

ለተግባራዊነቱም  ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ወጣቱ አካላዊና አዕምሯዊ አቅሙን በተገቢው መንገድ ለራሱ፣ ለሀገሩ እድገትና ብልጽግና እንዲያውል ለሚደረገው የስብዕና ግንባታ ስራ ውጤታማነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ወጣቶች ቀን ዋነኛ ዓላማ ወጣቶች እርስ በእርስ ተቀራርበው በአገራቸው ብሎም በአህጉራቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት የተሻለ አገርና አህጉር ለመፍጠርና ለማጽናት ቃል ኪዳናቸውን እንዲያድሱ ማስቻል መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው ወጣቶች ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጠናከር ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ተሳትፏቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ አክለው ወጣቶች በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች  ተጨባጭ ለውጦችን ለማምጣት ዘመኑ በደረሰባቸው እሳቤዎችና ቴክኖጂዎች እራሳቸውን ለማብቃት  በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

“ወጣቶችን ከአልባሌ ተግባር ለመታደግ በመንግስት በኩል የአገልግሎት ማዕከላትን ማስፋት ይገባል” ያለው ደግሞ የበዓሉ ታዳሚ  ወጣት ተስሏች ቶንሩድ ነው።

ሌላው ወጣት ጌትነት አድማሱ በበኩሉ የቀኑ መከበር ወጣቶችን በማቀራረብ ለአገራቸው ሰላምና ልማት በአንድነት ለመስራት ያነሳሳል “ብሏል።