ምክር ቤቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ

576

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ህዳር 13/2015/ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በመወያየት ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

በዛሬው መደበኛ ስብሰባው የምክር ቤቱን 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ እና 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ-ጉባዔዎችን በመመርመርም በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቢዎች ሚኒስትር ሆነው ቀደም ብለው የተሾሙትን ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ ሹመትም  በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

የመከላከያ ሠራዊት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን በውሳኔ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 09/2015 ዓ.ም በመመርመር ለዝርዝር ዕይታ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 8/2015 ዓ.ም መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የዜጎች መብት መከበሩን፣ የሕግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ መልካም የመንግሥት አስተዳደርን ለማስፈን የተቋሙን የአሰራርና የሕግ ክፍተት መፈተሽ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሥራ ላይ የሚገኘውን አዋጅ ቁጥር 1142/2011 በማሻሻል የተቋሙን ኃላፊዎችና አደረጃጀት በማጠናከር ስኬታማ ሥራ እንዲያከናውን ለማድረግ አዋጁን ማሻሻል እንዳስፈለገ አብራርተዋል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ቋሚ ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፤ የመከላከያ ሠራዊትን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ በተመለከተ ለምክር ቤት አባላት አቅርበዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የማሻሻያ እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት መካከል የመከላከያ ሠራዊት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሠራዊቱ አገራዊ ኃላፊነቱን በአስተማማኝ መልኩ እንዲወጣ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ በፊት አዋጁ ማሻሻያ እንደተደረገበት አስታውሰው፤ አሁንም ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች በመኖራቸው ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም የቀረቡላቸውን የሹመት የውሳኔ ሃሳብ፣ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጆች እና የፌደራል ዳኛ ስንብትን አስመልክቶ የተለያዩ ሃሳብና አስተያየቶችን በመስጠት በሙሉ ድምጽ ለየቋሚ ኮሚቴው መርተዋል።

ኢትዮጵያን በመስዋዕትነቱ እያጸና የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተነሳሽነት ለማሳደግ በሚሻሻለው አዋጅ ውስጥ የሠራዊት ቀን እንዲካተትም ጠይቀዋል።

ሠራዊቱ የሚከፍለውን መስዋዕትነት በሚመጥን መልኩ በሥራ ላይም ሆኖ ከሥራ ሲሰናበት ክብሩን የሚመጥን ሃሳብ በአዋጁ መካተት እንዳለበትም አመላክተዋል።

በሌላ በኩል የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ፋንታሁን ደለለ ሽፈራው፤ በቀረበባቸው የዲሲፕሊን ግድፈት የስንብት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቶ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም