የሳይበር ሉዓላዊነትን በዘላቂነት ለመጠበቅ የባለተሰጥኦ ታዳጊዎችን አቅም በማጎልበት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው

168

ሕዳር 13/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሳይበር ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለመጠበቅ የባለተሰጥኦ ታዳጊዎችን አቅም በማጎልበት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።

ታዳጊ ሞሂቦን ኢብሳ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ ለሶፍትዌር ፈጠራ ስራ የተለየ ፍቅር እንዳለው ይናገራል፡፡

የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመከታተልና መረጃዎችን በማንበብ ህልሙን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ነው የገለጸው፡፡

ለፈጠራ ስራዎች ውጤታማነት የተቋማት እገዛ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጾ፤ ከዚህ አኳያ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ስር በሚገኘው የሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል ባገኘው ድጋፍ  የተለያዩ መተግበሪያዎችን መስራት መቻሉን ተናግሯል፡፡

በተለይ የትምህርት ቤት አስተዳደር ስርዓት መተግበሪያው በሚማርበት ትምህርት ቤት ጥቅም ላይ መዋሉን  ያነሳው ታዳጊው፤ ማእከሉ ለባለተሰጥኦ ወጣቶች የፈጠራ ስራ ቁሳቁስን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ብሏል፡፡

በማዕከሉ ያሉ ባለሙያዎች እርሱን ጨምሮ ለታዳጊዎች ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

በተመሳሳይ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ዳግም አበበ እና የ12 ተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ለሁሉም ቁምላቸው ወደ ማዕከሉ ከመጡ ወዲህ ለሙያቸው መዳበር የሚሆኑ ስልጠናዎችን እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማእከሉ በተለይ ወጣቶች እርስ በርስ ልምድ እንዲለዋወጡ እድል የፈጠረ መሆኑንም አንስተው በዘርፉ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎችም ወደ ማዕከሉ በመምጣት የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት ለማስጠበቅ የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ልማት ማዕከል ኃላፊ አቶ ካሳሁን ደሳለኝ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ አሁን ላይ ለ120 ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

የማዕከሉ ሰራተኞች ወደ ትምህርት ቤቶች በመሄድ ጭምር ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች ለይተው ወደ ማዕከሉ እንዲሚቀላቀሉ እያደረጉ መሆኑንና ወደ ማእከሉ ለሚመጡ ታዳጊዎች የቁሳቁስና የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ክረምት ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ 60 ታዳጊዎች ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን አንስተው በቀጣይ ይህንን ስራ ለማስፋት ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ስምምነት መፈፀሙን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የሳይበር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ታዳጊዎች ላይ መሰረት ያደረገ ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ታዳጊዎች በድረገፅ cychallenge.insa.gov.et እንዲሁም ወደ ተቋሙ በመምጣት ተመዝግበው ተሰጥኦዋቸውን ማጎልበት እንደሚችሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም