በኦሞ ሸለቆ አዲስ የምርምር ማዕከል ሊቋቋም ነው- የጂንካ ዩኒቨርሲቲ

242

ጂንካ(ኢዜአ) ህዳር 13/2015 በአካባቢው ያለውን ዕምቅ የብዝሃ ህይወት አቅም አውጥቶ ለመጠቀምና ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለማዘጋጀት የሚያግዝ የምርምር ማዕከል በኦሞ ሸለቆ አካባቢ ሊቋቋም መሆኑን የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ማዕከሉን ለማቋቋም ከካናዳ፣አሜሪካ፣ ኬኒያ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት የተውጣጡ የብዝሃ ህይወት ተመራማሪዎች በሸለቆው አከባቢ የመስክ ምልከታ እያደረጉ ነው።

የምልከታው አላማ በአከባቢው "የኦሞ- ቱርካና የምርምር ማዕከል" የተሰኘ የጥናትና የምርምር ማዕከል በጋራ ለመመስረት ያለመ መሆኑን የጂንካ ዩኒቨርስቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤሊያስ አለሙ በተለይ ለኢዜአ ገልፀዋል።

የምርምር ማዕከሉ በአካባቢው ያለውን ያልተነካ ዕምቅ ሀብት መጠቀም የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን ማበርከት ቀዳሚው ዓላማ መሆኑን አብራርተዋል ።

በተለይም በእንስሳት፣ በአሳ ሀብት ምርት እንዲሁም በግብርናና በብዝሃ-ህይወት ላይ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ያካሂዳል ብለዋል ዶክተር ኤሊያስ ።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳትና ዓሳ ሀብት፣ ብዘሃ-ህይወት፣ ብዘሃ-ባህል እና አግሮ ኢንዱስትሪ ላይ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው የምርምር ማዕከሉ መቋቋም ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም ነው የገለጹት ።

ከተለያዩ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ማዕከላት ጋር በጋራ መስራት ዩኒቨርስቲው በልህቀት ማዕከልነት የሚሰራቸውን ተግባራት ለማሳካት አጋዥ እንደሆነም ተናግረዋል ።

በምልከታው ከአገር ውስጥ ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ፣አዲስ አበባና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ከውጭ ደግሞ ከካናዳ፣አሜሪካ-ሚቺጋን እና ኬኒያ-ማሴኖ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የብዝሃ ህይወት ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም