በክህሎት የታነጹ ተማሪዎችን ለማፍራት መምህራን አርዓያ በመሆን ትውልድ የመገንባት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል -ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና

182

ህዳር 12/2015(ኢዜአ) በክህሎት የታነጹ ተማሪዎችን ለማፍራት መምህራን አርዓያ በመሆን ትውልድ የመገንባት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና አስገነዘቡ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ኮሌጆቹ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎችና አሳታሚዎች እውቅና ሰጥቷል።

በእውቅና መርሃ-ግብሩ ላይ  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናን ጨምሮ  በተለያዩ የትምህርት መስኮች ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን ያከናወኑ ምሁራን ተገኝተዋል።

እውቅናው የምርምር ስራዎች አግባብ ባላቸው ጆርናሎች ያሳተሙ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ እና በማህበረሰብ አገልግሎት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምሁራኑ መሰጠቱ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በዚሁ ወቅት እውቅና የተሰጣቸው ምሁራን በጽንሰ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር እውቀት የተፈተኑ ብቁ ባለሙያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በክህሎት የታነጹ ተማሪዎችን ለማፍራት መምህራን አርዓያ በመሆን የተሰጣቸውን ትውልድ የመገንባት ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በክህሎት የታነጹ ተማሪዎችን ማፍራት እንዲቻልም መምህራን በምርምር ስራዎች እንዲሳተፉ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ምሁራኑም የተሰጣቸው እውቅና ተጨማሪ ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ለማህበረሰቡ ማቅረብ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ምትኬ ሞላ፤  የተሻለ አፈፃጸም ያስመዘገቡ ከ700 በላይ ተመራማሪዎች ለእውቅናው እንደተመረጡ ገልጸዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ዩንቨርሲቲው ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት በታወቁ መጽሄቶች ላይ የምርምር ስራዎቻቸውን ያወጡ ምሁራን ተመርጠው ለሽልማት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

እውቅና የተሰጣቸው ምሁራን በበኩላቸው  ጥናት የትብብር ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር በትብብር መንፈስ መስራት በመቻላቸው ለእውቅና መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ወጣት ተመራማሪዎች የእነርሱን ፈለግ በመከተል በትብብር የተሻለ ስራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ እውቅና ከተሰጣቸው ተመራማሪዎች በተጨማሪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ባለፉት ስድስት ወራት  በኢኮኖሚክስ ዘርፍ 14 የምርምር ጽሑፎችን በማሳተም እውቅና ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም