በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር ለሁሉም የምትመች አገር ለመገንባት የጋራ ትብብር ያስፈልጋል- የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ

208

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 12 ቀን 2015  በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር ለሁሉም የምትመች አገር ለመገንባት የጋራ ትብብር ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ አባላት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት ከኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ አባላት ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት እና ቀጣይ ስራዎች ገለጻ ተደርጓል።

የመድረኩ ተሳታፊ የአገር ሽማግሌዎች ለኢዜአ እንዳሉት ሀገራዊ ምክክር የአገር ሕልውና የሚፈታተኑ ተቃርኖዎችን የሚያስታርቅ፣ አለመግባባትን በምክክር ዕልባት የሚሰጥና አገርን በጽኑ መሰረት ላይ የሚያቆም ነው።

የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ ሰብሳቢ ዶክተር ተስፋጽዮን ደለለው፤ ኢትዮጵያን ለመጭው ትውልድ እናውርስ ካልን 'ምስቅልቅሏ የወጣች ወይስ የሰከነች አገር?' ብለን መጠየቅ ይገባናል ይላሉ።

ለኢትዮጵያ ሲባል ከዕድሜዬ ቢቀነስ በወደድኩ የሚሉት ዶክተር ተስፋጽዮን፤ ሰላሟ የተጠበቀና የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለአዲሱ ትውልድ ለማስረከብ ችግሮችን  በምክክርና ውይይት መፍታት ይገባል ብለዋል።

ከመማክርት ጉባኤው አባላት መካከል መላከ ጥበብ ስሜነህ አበበ፣ አባ ገዳ ሰንቦቶ በየነ እና ወይዘሮ ማሪያ ሙኒርም አባቶች መስዋዕትነትን በመክፈል ጭምር ያስረከቡንን አገር ሉዓላዊነቷን ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረክብ ይገባል ብለዋል።

የሀሳብ ልዩነቶችን በምክክር ወደ ጋራ በማምጣት፤ ጠንካራ አገረ መንግስት መገንባት እና አገርን ወደ ልማት ጎዳና ማስገባት ከሁሉም ህብረተሰብ ክፍል እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን በጎ ሚና በመጠቀም ችግሮች በምክክር ተቀርፈው አገር በጽኑ መሰረት ላይ እንድትጸና እንደሚሰሩም የአገር ሽማግሌዎቹ  አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዳሉት ኮሚሽኑ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን ያለመግባባት እና ለሀገር ዕድገት ሳንካዎችን በምክክር ወደ መግባባት ማመጣት ነው።

የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች በህዝብ ዘንድ መቻቻልና ሰላም በመፍጠር ሀገራዊ ስርዓትን እንዲቀጥል ለዘመናት የሰሩ የአገር ባለውለታዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑም አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ከተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶች እንደሚሰራ ገልጸው፤ ከነዚህም መካከል የሀገር ሽማግሌዎች ቀዳሚዎቹ የኮሚሽኑ ስራ አጋዦች እንደሆኑ ገልጸዋል።

ከተቋቋመ ስምንት ወራትን ያስቆጠረው ኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፉን እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው፤ በክልልና በዞኖች ቅርንጫፎችን የመክፈት፣ አወያይና አመቻቾችን ለይቶ የማሰልጠን ቀጣይ ስራዎች ናቸው ብለዋል።

ከቀናት በፊትም ከ47 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች ጋር ተቋማቱ ለምክክሩ አጋዥ በሚሆኑበት ጉዳይ ላይ በመወያየት መግባባት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

የክልል ቅርንጫፎች እና የዞን ማስተባባሪዎች በቅርብ ጊዜያት እንደሚከፈቱም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም