በውጭ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችን የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

101

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 12/2015 በውጭ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችን የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከስደት የሚመለሱ ዜጎችን በዘላቂነትን የማቋቋሙ ስራ ላይም ትኩረት መደረጉን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከአንድ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በዛሬው እለት አዲስ አበባ ገብተዋል።  

ከስድት የተመለሱት ኢትዮጵያዊያን በሳዑዲ ያለመኖሪያ ፍቃድ በህገ-ወጥ መንገድ የሚኖሩ፣መኖሪያ ፍቃዳቸው ያለፈባቸውና በእስር ላይ የቆዩ ሲሆኑ፤የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡   

ሚኒስትር ድኤታዋ  በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በሳዐዲ አረቢያ የሚገኙ 100 ሺህ ዜጎችን ለመመለስ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።    

እስካሁን ከ71 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መመለስ መቻሉንና አብዛኛዎቹ  ወደ መጡበት አካባቢ ተመልሰዋል ሲሉ ገልጸው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ መጡበት አካባቢ መመለስ ያልቻሉት ደግም በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

ቀሪ 30 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን በመጠቆም በዛሬው እለት የተመለሱትም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ አምባሳደር ብርቱካን ገለጻ በውጭ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችንን መመለሱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

 ኢትዮጵያዊያን ከተመለሱ በኋላ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ዜጎች ከተመለሱ በኋላ የሥነ ልቦናን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።     

የስደተኞችና ስደት ተመላሾች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው ከስደት የሚመለሱ ዜጎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ላይ ተቋሙ እየሰራ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም በመጠለያ ውስጥ ያሉ ዜጎች የጤና፣ደረቅ ምግቦችን ጨምሮ መሰል ድጋፎች የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ሥራው በመንግሥት አቅም ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።   

ለኢዜአ አስተያተቻውን የሰጡ ተመላሾች በበኩላቸው ከአስቸጋሪ ሁኔታ ወጥተው ለአገራቸው በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልጸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ለአገራቸው እንዲበቁ አፋጣኝ ሥራ ሊሰራ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም