የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ግንባታቸው ሳይጠናቀቁ የቆዩ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት- ምክር ቤቱ

174

ህዳር 12/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ለረዥም ዓመታት ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ የቆዩ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ-ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣንን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ እንዳሉት፤ ባለሥልጣኑ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ አፈጻጸም ያስመዘገበ ቢሆንም ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለመፈጸም የሄደበት ርቀት አዝጋሚ ነው።

በአገሪቱ ግንባታቸው ሳይጠናቀቁ ከሁለት እስከ ስምንት ዓመት ያስቆጠሩ በርካታ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙ የጠቀሱት ሰብሳቢዋ፤ ለአብነትም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን  ሕንጻ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ የሰነዶች ማረጋገጫና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል ብለዋል፡፡

ሜጋ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ለአገልግሎት እየበቁ የሚገኝበትን ልምድ በመውሰድ ተቋሙ በተጓተቱ ፕሮጀክቶች ላይለውጥ ለማምጣት መሥራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ለዚህ ስኬት ይረዳው ዘንድ የሰው ኃይሉን በማሟላትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚያደርገውን ጥረት ቋሚ ኮሚቴው ክትትል በማድረግ እንደሚደግፍም ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ባለሥልጣኑ  የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮችንና አማካሪዎችን ልምድ በማሳደግ በኩል እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ሲሉ ገልጸው  በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታዩ ሙስናዎችን ለመከላከል ትኩረት መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ በበኩላቸው፤ ባለሥልጣኑ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአሰራር መመሪያዎችን በማሻሻል ባለፉት 3 ወራት አጠቃላይ አፈጻጸሙን ከ86 በመቶ በላይ ማድረሱን አስታውሰዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በሰው ኃይል አደረጃጀት፣ በበጀትና ቴክኖሎጂን በማበልጸግ የባለድርሻ አካላትን ድጋፍ እንደሚፈልግ ገልጸው ለዚህም ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ገንቢ አስተያየቶችን በማካተት በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚሰራም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም