ኢትዮጵያ ለጉብኝት የተመቸችና በርካታ የቱሪስት መደራሻ ያላት አገር መሆኗን እንደታዘቡ ቱሪስቶች ገለጹ

77
አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 ኢትዮጵያ ለጎብኚዎች የተመቸችና በርካታ የቱሪስት መደራሻ ያላት አገር መሆኗን መታዘብ እንደቻሉ ኢትዮጵያን እየጎበኙ ያሉ ቱሪስቶች ገለጹ። በመስቀል አደባባይ የደመራ በዓል አከባበር ላይ የተገኙ ቱሪስቶች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አገሪቷ ለጎብኚዎች የተመቸች አገር ናት። ኢትዮጵያን ለተወሰነ ዓመት እንደሚያውቃት የሚናገረው ፈረንሳዊው አና ኮፍማን ከአገሩ ፈረንሳይ ጋር የቆየ ወዳጅነት እንዳላት አስታውሶ ለኢትዮጵያ ልዩ ስፍራ በመስጠት የቱሪስት መዳረሻዎችን እንደሚጎበኝ ገልጿል። ''አሁን ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት በዚህ መስከረም ወር ውስጥ ብዙ በዓላት እንደምታከብሩ ስለማውቅ ነው'' ያለው ጎብኚው የመስቀል በዓል ደግሞ ደስ የሚል በዓል እንደሆነ ተናግሯል። ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ እጅግ ብዙ ተፈጥሯዊ መስህብ ያላትና ህዝቦቿም ተግባቢና መልካም መሆናቸውን እንደተረዳ ጠቅሷል። እና በኢትዮጵያ ቆይታው እስካሁን ያላያቸውን የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች ለመጎብኘት እቅድ መያዙንም ተናግሯል። ዛሬ ጠዋት ከጣሊያን አዲስ አበባ መግባቷን የምትናገረው ዳኒኤላ ጊባ አገሯ እያለች ስለ ኢትዮጵያ ብዙ አጓጊ ነገሮችን ሰምታ መምጣቷን ገልጻለች። ከዚህ በፊት ብዙ የአፍሪካ አገሮችን መጎብኘቷን የገለጸችው ዳኒኤላ ''ኢትዮጵያን ተዟዙሬ ለማየት ቸኩያለሁ'' በማለት ያላትን ጉጉት በመግለጽ ከነገ ጀምሮ ባህር ዳር፣ አክሱም፣ ላሊበላና በመረጨሻም አዲስ አበባን በደንብ ለመጎብኘት እቅድ እንዳለት ጠቁማለች። እስራኤላዊው ዶክተር ሳሙኤል ኪፍሆም ስለኢትዮጵያ በርከታ ነገሮች እንደሚያውቁ ገልጸው ወደኢትዮጵያ መጥተው ከጠበቁት በላይ ሊመለከቱ መቻላቸውን ተናግረዋል። ሁለቱ አገሮች በቤተ እስራኤላውያን አማካኝነት የተሳሰሩ በመሆናቸው በኢትዮጵያ ቆይታቸው እጅግ ደስተኛ ሊሆኑ እንደቻሉ ገልጸዋል። በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ጉብኝት ላይ የምትገኘው እስራኤላዊቷ ዩዲያ ጋቢድም እንዲሁ በቆይታዋ እጅግ የተደሰተች መሆኗን ገልጻለች። ዩዲያ እንደምትለው ኢትዮጵያውያን እጅግ ውቦችና የሚደዱ ህዝቦች እንዲሁም ህዝቡ በጎነት የሚታይበት መልካም ሰው መሆኑን አብራርታለች። ጎብኚዋ አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ልማትና ሰላምም ለቆይታቸው ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ተናግራለች። በየዓመቱ በመላ አገሪቱ በሚከበረው የመስቀል በዓል ላይ በርካታ ቱሪስቶች የሚገኙበትና ዋና የቱሪስት መስህብ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም