የእናቶችና ጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ቅንጅታዊ አሰራር ሊያጠናከር ይገባል

306

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 12 ቀን 2015  በወሊድ ወቅት የሚከሰት የእናቶችና ጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ባለድርሻ ተቋማት ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ፡፡

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ  ጤና ኢንስቲትዩት በእናቶች እና ጨቅላ ህጻናት ሞት ቅኝት እና ምላሽ ስርዓት ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በመድረኩም የእናቶች ሞት ቅኝት እና ምላሽ ስርዓት በ2006 ዓ.ም መጨረሻ  እንዲሁም የጨቅላ ህጻናት ሞት ቅኝት እና ምላሽ ስርአት ደግሞ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ መሆኑ ተገልጿል።

የአሰራር ስርዓቱ የእናቶችና ህጻናት የጤና መረጃ  እና የጥራት ማሻሻያ ሂደት ሲሆን፤ ከማህበረሰብ ጀምሮ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ የሚያገናኝ የክትትል አይነት መሆኑም ተጠቅሷል።

የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አስቻለው ዓባይነህ አሰራሩ በወሊድ ጊዜ ለሚከሰት ሞት ምክንያት የሆኑ አንኳር መንስኤዎችን በመለየት ሞትን ለመቀነስ እንዲቻል ያለመ ነው ብለዋል።

ስርዓቱ ከሶስት አራተኛ በላይ በሚሆኑ የጤና ተቋማት ላይ እየተተገበረ ቢሆንም የእናቶች ሞት መለየት እና የማሳወቅ፣ መረጃዎችን በመተንተን ሪፖርት የማድረግ እንዲሁም  የእናቶች ሞትን ለመከላከል መደረግ ያለባቸው ዝግጅቶችን ከማቀድ አኳያ ክፍተቶች ታይተዋል ነው ያሉት።

ለአሰራር ስርዓቱ ራሱን የቻለና በቂ በጀት የመደቡ ተቋማት ቁጥር አናሳ መሆኑን  አንስተዋል።

መንግስት በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችንና ጨቅላ ህጻናትን ቁጥር ለመቀነስ ጥረት እያደረገ ቢሆንም አሰራሩ በአግባቡ አለመተግበሩ እንደ ሀገር በ2030 የእናቶችና ህጻናት ሞት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የተያዘው ግብ እንዳይሳካ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት የሞት ምጣኔውን አሁን ካለበት 14 ሺህ ወደ 279 ዝቅ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2030 የእናቶችና ህጻናት የሞት ምጣኔን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ተቋማት በተቀናጀ መንገድ እርምጃቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ከሚከሰቱ የእናቶች ሞት ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት መከላከል የምንችላቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህም ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚሸፍነው የደም መፍሰስ ችግር በመሆኑ ችግሩን ለመቀነስ የተቋማት ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለዚህም ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ አጋር አካላትም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም