“እናት ስትታመም አልጠይቅም የሚል ልጅ እንደሌለ ሁሉ ሀገራችን በጠራችን ጊዜ አቤት በማለት የተቻለንን ድጋፍ እናደርጋለን” ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን

149

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 12 ቀን 2015 “እናት ስትታመም አልጠይቅም የሚል ልጅ እንደሌለ ሁሉ ሀገራችን በጠራችን ጊዜ ሁሉ አቤት በማለት የተቻለንን ድጋፍ እናደርጋለን” ሲሉ በጣልያን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።

በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ በሮም ከሚገኙ ዳያስፖራ አደረጃጀት ተወካዮች ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተፈጠረውን ግጭት በሰላም ለመቋጨት የተፈረመውን ስምምነት በተለመከተ ማብራሪያ መሰጠቱ ተገልጿል።

በጣልያን የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ ሀገር ተጋርጦ የነበረው አደጋ እንዲያበቃ በፕሪቶሪያ በመንግስትና በሕወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና የኢትዮጵያን ልማት ለማፋጠን የሁሉም ወገን ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ እያደረገ ላለው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አምባሳደሯ ምስጋናቸውን አቅርበው ቀጣይነት ባለው መልኩ በሀገሩ ልማት ላይ አዎንታዊ አሻራውን ለማሳረፍ የጀመራቸውን ድጋፎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በበኩላቸው እናት ስትታመም አልጠይቅም የሚል ልጅ እንደሌለ ሁሉ አገራቸው በጠራቸው ጊዜ ሁሉ አቤት በማለት የተቻላቸውን ሲያደርጉ የቆዩትን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

በቀጣይ ጊዜያትም ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ለልማት ጉዞው የበኩላቸውን እንደሚያበረክቱ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም