የመስቀል በዓል የብርሃንና የሠላም ተምሳሌት በመሆኑ ለአንድነትና ለሰላም በጋራ የምንቆምበት ነው – የበዓሉ ታዳሚዎች

1588

አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 የመስቀል በዓል የብርሃንና የሠላም ተምሳሌት በመሆኑ ለአንድነትና ለሠላም በጋራ የምንቆምበት ነው ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናገሩ።

የመስቀል ደመራን በዓል ለመታደም በመስቀል አደባባይ የተገኙትና ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች አገሪቱ በአዲስ ለውጥ ላይ ባለችበት ወቅት የሚያከብሩት በዓሉ የተለየ ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ከግብ እንዳይደርስ ፈተና እየሆኑ የመጡትን የዘርና የጥላቻ አዝማሚያዎች ተባብረን ልናስወግድ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

መሪጌታ ጥላሁን ዳምጠው የተባሉ ታዳሚ መለያየት ፣ ዘረኝነት፣ መከፋፈል አያስፈልግም፣ በአንድነት ፣ ወንድማማች ሆነን ሁሉም ሳይከፋፈል በአንድ ላይ ሆኖ ኢትዮጵያ መጀመሪያም አብሮ በመብላት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመፈቃቀር የምትታወቅ ናት ይሄ እንዲቀጥል ብዬ አሳስባለሁ በእኔ በኩል ቤተ ክርስቲያንም ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት ነው የምታስተምረው ብለዋል።”

በዓሉ ላይ ያገኘናቸው ሌላው ታዳሚ አቶ ጌታቸው በዳኔ በበኩላቸው አንድነትን በማጠናከር ከጥላቻ ፣ ከዘረኝነት፣ ከምቀኝነት፣ ከተንኮል በሃሰት ሰውን ከመተንኮል በሃሰት ሰውን ከማሰር ከዚህ ሁሉ ድነን ከዚህ ሁሉ በመውጣት በፍቅር መቆም አለብን ብለዋል፡፡

በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚናፈሱ ብሄርን ከብሄርና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ መረጃዎች እየበዙ በመሄዳቸው አስተዋይና ምክንያታዊ በመሆን ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።

እንደ አገር የመጣው ለውጥ ዴሞክራሲያዊ መብትን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ አገርን የሚያሳድግና ሁሉንም የሚያግባባ መሆኑን በመጥቀስም ነፃነቱን ከስሜታዊነት በፀዳ መንገድ መጠቀም ይገባል ብለዋል።