የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የሱዳን ጠቅላላ የደህንነት አገልግሎት በጋራ ለመስራት የሚስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

123

ህዳር 12/2015 በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ ከሱዳን ጠቅላላ የደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አህመድ ኢብራሂም አሊ ሙፍዲል እና ሌሎች ከፍተኛ የተቋሙ አመራሮች ጋር በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በካርቱም መክረዋል ።

ሁለቱ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ግንኙነታቸውን አጠናክረው በጋራ መስራት ለሁለቱ ጎረቤት ሀገራት እና ህዝቦች ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ስለሚኖረው ጉልህ አስተዋጾ በጥልቀት መምከራቸውም ተገልጿል።

ከውይይቱ በኋላም ሁለቱ ተቋማት የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መረጃ ለመለዋወጥና በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ተጠቅሷል ።

የስምምነቱ ትኩረት ተቋማቱ በጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሞክሮ እና መረጃ ለመለዋወጥ፣ የቀጠናው የጋራ ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነት በጋራ መዋጋት ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል፣ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ ደህንነትን ማረጋገጥ እና የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ሰላም የሚጎዱ አካላትን በጋራ መከላከል ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ነው የተገለጸው።

በአቶ ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት የልዑካን ቡድን በካርቱም ለሁለት ቀናት በነበረው ይፋዊ የስራ ጉብኝት ከሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱል ፈታ አልቡራሃንና ከሉአላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ሞሐመድ አምዳን ዳጋሎ ጋር ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት ሰላምና ደህንነት ዙሪያ መወያዩቱን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም