22ኛው የዓለም ዋንጫ ኳታርን ከማስተዋወቅ ባለፈ አለም ዓቀፍ አንድነት የሚጠናከርበት ነው --የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ

225

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 22ኛው የዓለም ዋንጫ በመካከለኛው ምስራቋ ኳታር መካሔዱ ባህሏንና ጥበቧን ከማስተዋወቅ ባለፈ ዓለም አቀፍ አንድነትን ለማጠናከር የሚረዳ እንደሆነ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ።

“የ2022 የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ እድሉን ስላገኛቹህ እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት ደስታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ባህልን ከማስተሳሰር ባሻገር የጋራ አንድነትን የሚያጠናክር እንደሆነ ተናግረዋል።

የአስተናጋጇን አገር ህዝብም ከቀሪው የዓለም አገራት ጋር በማቀራረብ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ያጠናክራል ብለዋል።

ኢትዮጵያም የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗን ገልጸው ዛሬ የተጀመረው የ2022 የዓለም ዋንጫም የተሳካ እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር ሐመድ አል ዶሳሪ፤ በበኩላቸው አገራቸው ኳታር 22ኛውን የዓለም ዋንጫ በድምቀት ለማካሄድ ሰፊ ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷን ተናግረዋል።

በተደረገው ዝግጅትም የዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ ሃገራት ብሔራዊ ቡድኖች ተጫዋቾች፣ ደጋፊዎች እና እንግዶች በኳታር ጥሩ ቆይታ እንደሚኖራቸውም ገልጸዋል።

በኤምባሲው በተከናወነው የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታዋ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም