በበጀት አመቱ ከ285 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ የ29 ድልድዮች ግንባታ ይከናወናል-ቢሮው

158

ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 በተያዘው በጀት አመት ከ285 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ የ29 ድልድዮች ግንባታ እንደሚከናወን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ አስታወቀ።

በምስራቅ ጎጃም ዞን በቢቡኝ ወረዳ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት ግንባታው የተጠናቀቀ ድልድይ ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ቀለሙ ሙሉነህ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታ ለማረጋገጥ የመንገድና ድልድይ መሰረተ-ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው።

በተያዘው በጀት አመትም ከ285 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እያንዳንዳቸው 12 ሜትር ርዝመት ያላቸው 29 ድልድዩች ግንባታ ይከናወናል ብለዋል።

በክልሉ የተፋጠነ ልማት እንዲኖር ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ መንገዶችን ለመገንባት ባለፉት ጊዜያት በተደረገ እንቅስቃሴ ከ30 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው መንገዶች መገንባታቸውን ተናግረዋል።

ከተገነቡት ውስጥ ከ12 ሺህ 660 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው መንገዶች በወረዳ ገጠር መንገድ ፕሮግራም የተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በነዚሁ መንገዶች 2 ሺህ 662 ቀበሌዎችን እርስ በእርስ ማገናኘነት መቻሉን አመልክተዋል።

 የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው ''የጅያ'' ድልድይ አራት ቀበሌዎችን የሚያገኘኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ለድልድዩ ግንባታ ወጭ ከተደረገው 15 ሚሊዮን ብር ውስጥ 8 ሚሊዮኑ በመንግስትና 7 ሚሊዮኑ ደግሞ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተሸፈነ መሆኑን አመልክተዋል ።

በቀጣይም መሰል ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የመንግስትን አቅም ከህብረተሰቡ መዋጮ ጋር በማስተባበር ግንባታው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ከዚህ በፊት ለወንዙ መሻገሪያ በየዓመቱ የሚገነቡ የእንጨት ድልድዮች በየጊዜው በውሃ እየተወሰዱ በነዋሪው ላይ ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል" ያሉት ደግሞ የገነቴ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገዳሙ ታመነ ናቸው።

''የጅያ'' ድልድይ በተሻለ ደረጃ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ መደሰታቸውን ጠቅሰው "ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን ችግር ሙሉ በሙሉ የፈታ ነው" ብለዋል።

''ከዚህ በፊት በክረምት ወደ ዲጎ ጺወን ከተማ በመሄድ ጉዳይ መፈጸም የማይታሰብ ነበር'' ያሉት ደግሞ የቃጣ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እናቴነሽ ሙላት ናቸው። 

ቀደም ሲል በወንዙ ላይ የሚገነቡ የእንጨት ድልድዮች ስለማይቆዩ በሽተኛም ሆነ ወላድ እናቶችን በክረምት ወደ ህክምና ተቋም ለማድረስ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው "አሁን ላይ ችግሩ በመፈታቱ ተደስተናል" ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም