የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ለይቶ መስራት አስፈላጊ ነው - ዶክተር ሙላቱ ተሾመ

162

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ ለማስቀጠል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች በአግባቡ ለይቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት ለሚወክሉ መካከለኛና ነባር ዲፕሎማቶች ሱሉልታ በሚገኘው የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ እና የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ልምድና ተሞክሯቸውን በዚሁ ስልጠና እየተሳተፉ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች አካፍለዋል።

ኢትዮጵያን ወክለው የሚሰሩ ዲፕሎማቶች ሁሉ በአገር ፍቅር ስሜት ለአገራቸው ብሔራዊ ጥቅም መከበር በታታሪነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።

የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ልምዳቸውን ባካፈሉበት ወቅትም ዲፕሎማሲ ለአገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር በትጋት መስራትን የሚጠይቅ የስራ ዘርፍ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ ለማስቀጠልም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮችን በመለየት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ብሔራዊ ጥቅም ከንግግር ባለፈ በብርቱ ጥረት የሚረጋገጥ በመሆኑ ዲፕሎማቶች ራሳቸውን በከፍተኛ ኃላፊነት ማዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራተን አድንቀው፤ በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ጉርብትናን ማስቀጠል ጊዜው የሚጠይቀው ስራ ነው ብለዋል።

የዲፕሎማሲ ወዳጅነትን በማጎልበትም ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራት ሊኖራት የሚገባን ብሔራዊ ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ውጤታማ ስራ ማከናወን ተገቢ እንደሆነ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም