የሌማት ትሩፋት የማህበረሰቡን የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓት ለማሳደግ ያግዛል-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

382

ሀረር (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 በአረንጓዴ አሻራና በስንዴ ምርት እየታየ ያለውን ለውጥ በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በማጠናከር ማህበረሰቡ የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓት እንዲያዳብር እንሰራለን ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የሀረሪ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ዛሬ በይፋ አስተዋውቀዋል፡፡

አቶ ኦርዲን በድሪ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የሌማት ትሩፋት በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ ምርትና በአቮካዶ ምርት እየተመዘገቡ ላሉ ለውጦች ቀጣይ ምዕራፍ ነው፡፡

ማህበረሰቡ ካለው ምርት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት የሚችል ቢሆንም በተለይም በስርአተ-ምግብ ላይ ያለው ግንዛቤ ላይ አሁንም መሰራት ያሉባቸው ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በስርዓተ-ምግብ ራስን ከማስቻል ጀምሮ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት በዶሮ፣ በወተት እንዲሁም በማር ምርት ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህም ከውጭ የሚገቡ  የምግብ ሸቀጦችን በመተካት የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት የሁሉንም ትኩረት እና ርብርብ ይፈልጋል ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ እያንዳንዱ አመራር የበኩሉን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው መርሃ-ግብሩ እስከ ቀበሌ የሚወርድ እንደመሆኑ በርብርብ ውጤት ልናስመዘግብበት ይገባል ብለዋል፡፡

የእንስሳት እርባታውን በማስፋት ለስራ ዕድል ፈጠራ ሁኔታዎች የሚመቻቹበት መንገድ ይፈጠራል ሲሉም ገልፀዋል፡፡

በተለይም በእንስሳት ርባታ ላይ ዝርያ ማሻሻል፤ የመኖ አቅርቦት እና የእንስሳት ጤና ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶበት የሚሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎች በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የወተት እና የዶሮ ርባታ ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልከተዋል፡፡

በመስክ ምልከታውም በዘርፉ ተሰማርተው ለሚገኙ አካላት አስፈላጊው ድጋፍ የሚደረግበት መንገድ ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም