ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር አንድነትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው-የውድድሩ ተሳታፊዎች

152

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር አንድነትን ለማጠናከርና የሩጫ ባህልን ለማዳበር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የወድድሩ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም ከሚከናወኑ የጎዳና ላይ ታላላቅ ውድድሮች መካከል ከአፍሪካ በቀዳሚነት በዓለም አቀፍ ደግሞ በስድስተኝነት የሚጠቅስ ውድድር ነው።

ዛሬ በአዲስ አበባ የተከናወነው 22ኛው ዙር የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ የቀጠለ ውድድር ሲሆን ወደ ቱሪስት መስህብነትም እየተሸጋገረ የመጣ መድረክ ነው።

መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ባደረገው በዚህ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ከውጭ ሀገራት የመጡ አትሌቶችን ጨምሮ 40 ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል።

በውድድሩ ያገኘናቸው ተሳታፊዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዘ ጥቅም አለው ብለዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ የተሳተፈችው ሰሚራ ሁሴን በዘንድሮው ውድድር በርካታ ተሳታፊዎች  እንደነበሩ ጠቅሳ፤ ሰዎች እየተዝናኑ ጤናቸውን የሚጠብቁበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሳለች።

ሌላኛዋ ተሳታፊ ህያብ ፀጋአምላክ በበኩሏ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሰዎችን ለማቀራረብና አንድነትን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልፃለች።

በውድድሩ የተሳተፈው ጌታሰው ይልቃል ውድድሩ በኢትዮጵያ የሩጫ ባህልን በማዳበር በአንድ በኩል ጤናን ለመጠበቅ በሌላ በኩል ደግሞ ተወዳዳሪ አትሌት ለማፍራት ስለሚጠቅም ሊበረታታ ይገባል ነው ያለው።

በአዲስ አበባ ከተማ የቱሪስት መስህብ ከሆኑ ሁነቶች አንዱ “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” ላለፉት 20 ዓመታት በቀጠለው ውድድር ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

በተሳታፊዎች መካከል ጠንካራ ወዳጅነት የሚመሰረትበትና የመዲናዋ አንዱ የመዝናኛ አውድ ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል።

የዛሬውን በይፋ ካስጀመሩት የክብር እንግዶች መካከል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ታላቁ ሩጫ ለከተማችን ከስፖርታዊ ውድድርነቱ ባሻገር የአብሮነት፣ የሰላምና የፍቅር እንዲሁም የትብብር ተምሳሌት ጭምር ነው ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም