ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የትምህርት አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል-ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ

272

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 10/2015 የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት የትምህርት ማህበረሰቡ በተለይ አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት አለበት ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ አሳሰቡ።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለሦስት ቀናት የተካሄደው 31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ተጠናቋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እንደገለጹት በትምህርት ጥራት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የሚሰሩ ሥራዎች ውጤት እንዲያመጡ የመስኩ ባለሙያዎችና አመራሮች ሚና ከፍተኛ ነው።

"ሀገር ለማዳን በሚከፍለው መስዋዕትነት ልክ ትምህርቱን ከወደቀበት ማንሳት የእዚህ ትውልድ ሃላፊነት ነው" ሲሉ አመልክትዋል።

"በጉባኤው የታየው የትምህርት ማህበረሰቡ ቁርጠኝነት ተስፋ ሰጪ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፣በቀጣዮቹ ዓመታት የትምህርት ስርዓቱን በመሰረታዊነት መቀየር የሚያስችል ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር በርሀኑ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በትምህርት ዘርፍ ያጋጠመው ክፍተት ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ የከተተ መሆኑን አንስተዋል።

ጉባኤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከሩን ጠቁመው፣ በእዚህም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ለማፍራት በሚያስችሉ ጉዳዮች መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ የጋራ መግባባት በተደረሰባቸው ጉዳዮችና በአዲሱ የትምህርት ስርዓት ላይ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም