በኦሮሚያ ክልል 200 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ዘር ተሸፈነ

146

አዳማ /ኢዜአ/ ህዳር 10/2015 በኦሮሚያ ክልል 200 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ዘር መሸፈኑን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለጹ።

በክልሉ ምስራቅ ሸዋ ዞን ዋቄ ሚኣ ቀበሌ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በክልል ደረጃ ዛሬ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ቢካሄድም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ቀደም ብሎ መጀመሩ ይታወቃል።

ምክትል ፕሬዘዳንቱ አቶ አወሉ አብዲ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በተያዘው በጋ በክልሉ ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለመሸፈን እየተሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅትም 200 ሺህ ሄክታር በዘር መሸፈኑን የገለጹት አቶ አወሉ አምና ከ600 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ተሸፍኖ እንደነበር አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግስት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በመተግበር በአጭር ጊዜ ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱን የገለጹት ምክትል ፕሬዘዳንቱ አሁን የታየው ውጤት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።

እቅዱን ለማሳካት የእርሻ ትራክተር፣ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች፣ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በሚፈለገው ደረጃ እየቀረበ መሆኑንም አንስተዋል።

በድህነት ላይ የተጀመረው ዘመቻ እንዲሳካ የስራ ባህል ከመለወጥ ጀምሮ ሕዝቡ ዘንድ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አንዱ የዘመቻው አካል መሆኑንም አስረድተዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ እንደገለጹት በዞኑ የዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 200 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን እየተሰራ ነው ብለዋል።

በእስከ አሁኑ ሂደት ከታረሰው 51 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 27 ሺህ ሄክታር በዘር መሸፈኑን ጠቅሰው በተለይ አርሶ አደሩ የመኽር አዝመራን ከመሰብሰብ ጎን ለጎን ለበጋ መስኖ ስንዴ የሚውል የእርሻ ማሳ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን እየተዘራ ያለው ስንዴ ከ90 እስከ 100 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ የሚደርስ መሆኑን ነው የገለጹት።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ በበኩላቸው በዞኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማሳካት ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና 300 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር እየቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዞኑ 10 ወረዳዎች በ136 ቀበሌዎች ላይ ልማቱ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ከእርሻ ጀምሮ አመራረቱን በተሟላ ቴክኖሎጂና የኤክስቴሽን አገልግሎት በመደገፍ ከ6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።

ከአምና ልምድ በመውሰድ ዘንድሮ ቀደም ብለው መጀመራቸው ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ነው የገለጹት።

ከዞኑ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ የሆኑት ቡርቄ ዋቀዮ በበኩላቸው በመኽር ካረሱት አንድ ሄክታር መሬት ላይ 75 ኩንታል የስንዴ ምርት ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

ለበጋ መስኖ አርሻው ካዘጋጁት 4 ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ሄክታር ዘርተው ቡቃያው በጥሩ ሄኔታ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በተለይ መንግስት በዘንድሮ ዓመት በናፍጣ የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ሞቶሮች፣ የእርሻ ትራክተሮች፣ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ በማቅረቡ ፈጥነው ወደ ዘር መዝራት መግባታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም