በአዲስ አበባ ለሚገነቡ የልማት ስራዎች ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

142

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 10/2015 በአዲስ አበባ ለሚገነቡ የልማት ስራዎች ባለሃብቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጠየቀ።

በቦሌ ክፍለ ከተማ በ90 ቀናት በ360 ሚሊዮን ብር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ለባለሀብቶች፣ መንግሥታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ  ተቋማት ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በዕለቱም ከባለሀብቶች፣ መንግሥታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ  ተቋማትና ከሌሎችም  133 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ለመስጠት ቃል ተገብቷል።

በ90 ቀናት ውስጥ የሚከናወኑና ፕሮጀክቶች የምገባ ማዕከላት፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎች፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት፣ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት ለማደስና ለመገንባት፣ የገበያ ማዕከላትንና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን ያካተተ ነው።

በዚሁ ወቅት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ እንዳሉት በከተማው በርካታ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

በመንግስት የተጀመሩና የታቀዱ የልማት ስራዎች ለታለመላቸው ዓላማ እስኪውሉ ባለሃብቶችና ሌሎች አካላት እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

አቶ ጥራቱ አያይዘውም ቀጣዩ ትውልድ መስጠትን፣ በጎነትንና መተሳሰብን እንዲለማመድ ዛሬ የምናደርገው መረዳዳትና አገር የመገንባት ስራ  ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው በበኩላቸው ባለሀብቶች ለፕሮጀክቶቹ ያደረጉት ድጋፍ የበለጠ ተግተን እንድንሰራ ያደርገናል ብለዋል።

በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ከፍ የሚያደርጉና የነገውን ትውልድ  የሚያንጹ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ባለሃብቶቹ በፍላጎትና በተቆርቋሪነት ለፕሮጀክቶቹ ደስተኛ ሆነው ላደረጉት ድጋፍ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

ባለሃብቶቹ የከተማውን ነዋሪ ችግር ለመፍታትና ከተማውን ለማስዋብ መንግስት እያከናወነ ባለው ዘርፈ ብዙ ተግባር ላይ  ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም