ባህር ዳር ዩኒቨርሲቱ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እየሰራ ነው

158

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 10/2015 ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን 409 የተለያዩ የምርምር ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የጤና ትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 252 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ሽፈራው በምረቃ ሥነስርአቱ ላይ እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ለምርምር ሥራው ግብ አስቀምጦ እየሰራ ነው።

ግቡን ለማሳካትም ከበርካታ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በመልካም አስተዳደር፣ በአካባቢ እንክብካቤና አጠቃቀም ላይ የተለያዩ ምርምሮችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 በአፍሪካ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባር ቀደም የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑንም ዶክተር ተስፋዬ አስረድተዋል።

ለእዚህም 409 የተለያዩ የምርምር ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከምርምር ሥራው በተጨማሪ በሴቶች አቅም ግንባታ፣ በነፃ የህግ አገልግሎት፣ በገጠርና በከተማ መሬት አያያዝና አጠቃቀም፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 252 ተማሪዎች ዛሬ ለ9ኛ ጊዜ ማስመረቁንም ዶክተር ተስፋዬ ተናግረዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ ከተመራቂዎቹ መካከልም 57ቱ የሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተሮች ሲሆኑ የተቀሩት

በተለያዩ የሕክምና ሙያዎች በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው።

በምረቃ ሥነስርአቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በበኩላቸው፣ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጤና ባለሙያዎች የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ የጤና ባለሙያዎች እጥረት ለመፍታት ከትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀራረብ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"በእዚህም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በ37 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሕክምና ትምህርት በመሰጠቱ በሁሉም ዘርፍ የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ ተችሏል" ብለዋል።

የዛሬው ምሩቃንም ወደሥራ ሲሰማሩ የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅና ለማሻሻል ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት የተመረቁት ዶክተር ደስታው ተገኘ በበኩላቸው፣ በተመረቁበት የሕክምና ሙያ ህዝብና ሀገራቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

"በተለይ እናቶችና ህፃናትን ከሞት ለመታደግ በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ቁርጠኛ ነኝ" ሲሉም አረጋግጠዋል።

"በሰለጠንኩበት የሙያ መስክ ያስተማረኝን ህብረተሰብ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ'' ያለው ደግሞ በሚድዋይፈሪ ሙያ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀው ይበልጣል ወርቄ ነው።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ቁጥራቸው 40ሺህ የሚጠጋ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም