አሜሪካ ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት እንድትመለስ ማድረግ አለባት - የአሜሪካ የኮንግረስ አባል ዶን ቤየር

166

ሕዳር 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአሜሪካ የኮንግረስ አባል ዶን ቤየር ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) ተጠቃሚነት እንድትመለስ ለአገራቸው መንግስት ጥያቄ አቀረቡ።

አጎዋ የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ትብብርን ያጠናከረ ቁልፍ መሳሪያ ነውም ብለዋል።

የኮንግረስ አባል ዶን ቤየር (ቨርጂኒያ, ዴሞክራቲክ ፓርቲ) ለአሜሪካ የንግድ ተወካይ አምባሳደር ካትሪን ታይ ባጸፉት ደብዳቤ የኢትዮጵያ መንግስት ከሕወሓት ጋር የተፈራረመውን ስምምነት ተፈጻሚ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በስምምነቱ አማካኝነት መንግስት ተኩስ በማቆምና ሰብአዊ እርዳታን ባልተገደበ መልኩ ተደራሽ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዚሁ መሰረት የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን ወደ የአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) የመመለስን ጉዳት ሊያጤነው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚ በነበረችበት ወቅት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ እድገት እንዲያሳይ፣ በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረና የሁለቱን አገራት የንግድ አጋርነት ለማሳደግ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ተጠቃሚነቷን ስታጣ በአጎዋ ጥላ ስር ምርታቸውን ወደ አሜሪካ ይልኩ የነበሩ ኩባንያዎች የማስፋፋፊያ እቅዳቸውን መተዋቸውንና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን መቀነሳቸውን ነው የኮንግረስ አባሉ ለአምባሳደር ካትሪን በጻፉት ደብዳቤ የገለጹት።

ኢትዮጵያን ከአጎዋ የማስወጣት ውሳኔ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ላይ መቀዛቀዝ እንዲታይ ማድረጉንም አመልክተዋል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚነት በድጋሚ መመለስ ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይት እንዲያደርግ ዶን ቤየር ለአምባሳደር ካትሪን ጥሪ አቅርበዋል።

በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት ኢትዮጵያን በፍጥነት ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት ይመልሳታል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

የ72 ዓመቱ ዶን ቤየር የቨርጂኒያ ግዛትን ወክለው እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ በኮንግረስ አባልነት እያገለገሉ ይገኛል።

በቅርቡ በተካሄደው የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ(ሚድ ተርም ኢሌክሽን) በኮንግረስ አባልነት በድጋሚ ተመርጠዋል።

ዶን ቤየር ‘የአሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ (ኤፓክ) የተሰኘው የፖለቲካ ተግባር ኮሚቴ በአጋማሽ ዘመን ምርጫ ይሁንታ ከሰጣቸው 34 እጩዎች መካከል ይገኙበታል።

በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅትም ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት ለመመለስ አበክረው እንደሚሰሩ መግለጻቸው ይታወቃል።

የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባል ዶን ቤየር የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ትብብር እንዲጠናከር ገንቢ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም ይነገርላቸዋል።

በሚኖሩበት ቨርጂኒያ ግዛት ከሚኖሩ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በየጊዜው ውይይት በማድረግ መልካም የሚባል ግንኙነት መገንባት ችለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም