በአገር አቀፍ ደረጃ 17 የሳይንስ ካፌዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

201

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2015 በአገር አቀፍ ደረጃ 17 የሳይንስ ካፌዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት የሳይንስ ካፌዎች ለመገንባት እቅድ መያዙን አመልክቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የሐዋሳ ሳይንስ ካፌ አዘጋጅነት የኢኖቬሽንና  ቴክኖሎጂ አውደ-ርዕይ ዛሬ በሐዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

አገር አቀፍ የሳይንስ ባህልን ማዳበር አላማ ያደረገው የሳይንስ ካፌ ፕሮጀክት ከአምስት ዓመት በፊት መጀመሩ ይታወቃል።

ካፌዎቹ በዲጂታልና በሕትመት የተዘጋጁ የሳይንስ መረጃዎችን የያዙ ሲሆን የፈጠራ አቅም ያላቸው ሰዎች በካፌው በመገናኛት የሳይንስ አውደ ርዕዮችን የሚያዘጋጁበት አማራጭ ፈጥሯል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)  የሳይንስ ግንዛቤና ባህል በሕብረተሰቡ ውስጥ በማዳበር ረገድ የሳይንስ ካፌዎች ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል።

በዚህ ረገድም ሚኒስቴሩ ከክልሎች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የሳይንስ ካፌዎችን በመገንባት እያንዳንዳቸው በቀን ለ100 ወጣት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ የሳይንስ ካፌዎች የቴክኖሎጂ ምርት ቦታ መሆን እንዲችሉና የተሻለ አደረጃጀት እንዲኖራቸው አስፈላጊውን ያደርጋል ብለዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ማዳበር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድም ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት የመማር፣ የማላመድና የመጠቀም አገራዊ አቅም እንዲያድግ በኢንዱስትሪዎች፣ በከፍተኛ የምርምርና የትምህርት ተቋማት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እውቀት የተደገፈ አምራችና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ያለው ዜጋ ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ፍሬያማ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል የስራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀገረፅዮን አበበ በበኩላቸው ቢሮ በስሩ ካለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት በክልሉ በጥናት ላይ የተመሰረተ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂን ለማፍለቅና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶና አርብቶ አደሩ እንዲሁም የኢንተርፕራይዞችን ፍላጎት ያማከለ ቴክኖሎጂዎችን በየኮሪደሩ ለማፍለቅ በየደረጃው ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዛሬው አውደ ርዕይ ላይ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች፣ ኢንተርፕራይዞችና ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤቶች የፈለቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለእይታና ለውድድር መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

እስከ ህዳር 11 ቀን 2015 በሚቆየው አውደ ርዕይ ላይ መኖ ማቀነባበሪያ፣ የዘይት መጭመቂያና የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖችን ጨምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለእይታ ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም