ለሠላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት ህብረተሰቡን በማስተባበር የድርሻችንን እንወጣለን - የምክር ቤቱ አባላት

91

አሶሳ፤ ህዳር 8 ቀን 2015( ኢዜአ) ፡ - የፌደራል መንግስትና ህወሃት ያደረጉት ስምምነት በሃገሪቱ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት የሚበጅ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ የክልሉን ህብረተሰብ በማስተባበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባላት አስታወቁ፡፡

ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ  ኢዜአ ካነጋገራቸው የክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ሙሳ አህመድ ፤  የክልሉ ህዝብ የልማቱ ተጠቃሚ የሚሆነው በሃገሪቱ ዘላቂ ሠላም ሲኖር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞም ሠላም ቀዳሚና አስፈላጊ ነው ፤ የፌደራል መንግስትና ህወሃት ያደረጉት  ስምምነት የሃገሪቱን ሠላም የሚመልስ ነው ብለዋል፡፡

ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ መርዬም አብዱራህማን፤ ስምምነቱ  ወደ ዘላቂ ሠላም ይመልሳል ብለዋል፡፡

ስምምነቱ ተግባራዊ ሆኖ በሠላሙና ልማት የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲጨምር እስከታችኛው የማህበረሰብ ክፍል ወርደው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በሠላም እጦት ከተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህብረተሰብ አንዱ ነው ያሉት ደግሞ  አቶ አልበሂት አማን የተባሉ የክልሉ ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡

ለዚህም በመተከልና ካማሽ ዞኖች  ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር የደረሰውን ጉዳት ለአብነት አንስተዋል፡፡

በሠላም እጦቱ መንገድን ጨምሮ የበርካታ መሠረተ ልማቶች ግንባታ መስተጓጎሉን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ የተፈጥሮ ሃብት ይዞ በድህነት እንዲቆይ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱም ይህን ችግር ይፈታል ብለዋል። 

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በፌደራል መንግሥትና ህወሃት  መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት አዛዥና የህወሃት ታጣቂዎች አዛዥ ስምምነቱ ተፈፃሚ በሚሆነባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በኬኒያ ናይሮቢ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም