በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሊዝ ፋይናንስ ተሰራጭቷል - ኢንስቲትዩቱ

108

አዳማ ህዳር 08/2015(ኢዜአ) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሊዝ ፋይናንስ መሰራጨቱን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ  የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ከክልሎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ እየገመገመ ይገኛል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታህ ዩሱፍ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢንተርፕራይዞች ሰፊ የስራ እድል የሚፈጠሩበት ዘርፎች ከመሆን ባለፈ የዜጎችን ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና የገቢ ስርጭትን እውን ለማድረግ ቁልፍ ሚና አላቸው።

ለኢንተርፕራይዞቹ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሊዝ ፋይናንስ ስርጭት መከናወኑን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ይህም በገበያ ትስስርና አማራጮችን በማስፋት ረገድ አበረታች ስራዎች እንዲሰሩ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በጥራት፣ በብዛትና በዓይነት መተካት እንዲችሉ ከስራ ማስኬጃ ጀምሮ በአቅም ግንባታ፣ በመስሪያና መሸጫ ክላስተሮች ዘርፈ ብዙ ድጋፎች እየተደረጉላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ለ241 ኢንተርፕራይዞች ከ660 ሚሊዮን ብር በላይ ስራ ማስኬጃ የተሰራጨላቸው ሲሆን፣ ለ3ሺህ 134 ኢንተርፕራይዞች ደግሞ 30 አይነቶች የሚሆኑ የግብዓት ፍላጎት መለየቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በ16 የማምረቻ ክላስተሮች የመንገድ፣ ውሃ፣ መብራትና ሌሎች መሰል የመሰረተ ልማቶች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ማሟላት መቻሉንም ገልጸዋል።

በዚህም የእንተርፕራይዞችን የማምረት አቅም ከማጎልበት ባለፈ ምርቶችን በጥራት፣ በአይነትና በብዛት በማምራት የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ግብ አስቀምጠን እየሰራን ነው ብለዋል።

በተለይም ከ1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁና ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የታገዱ 38 አይነት ምርቶች በሀገር  ውስጥ ኢንተርፕራይዞች እንዲመረቱ ለማስቻል አጋጣሚዎችን ለመጠቀም እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ያለንን አቅም አሟጠን በመጠቀም የተሻለ አቅም ያላቸው ኢንተርፕራይዞች በጥራትና በአይነት ተኪ ምርቶችን  ማምረት  እንዲችሉ ሁሉን አቀፍ የዘርፉ ሴክተሮችና ባለድርሻ አካላት ድጋፍና እገዛ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም