አባያ ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ለመታደግ የድርሻችንን እንወጣለን---የአርባምንጭ የህዝብ ንቅናቄ መድረክ ተሳታፊዎች

135
አርባምንጭ ግንቦት 11/2010 አባያ ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ለመታደግ በሚደረገው ዘመቻ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በአርባምንጭ ከተማ በተዘጋጀ የህዝብ ንቅናቄ መድረክ የተሳተፉ ነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት ገለፁ። በከተማው ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የንቅናቄ መድረክ በዘመቻው ህብረተሰቡን የሚያስተባብር ግብረሀይል በማቋቋም ዛሬ ተጠናቋል። ከተሳታፊዎች መካከል በአርባምንጭ የዶይሳ ቀበሌ አስተዳዳሪ መቶ አለቃ ዳኜ ጎባ እንዳሉት መድረኩ ሀይቁን ከአረም በማፅዳት ዘመቻው ተሳታፊዎች ድርሻቸውን እንዲለዩ አስችሏል ። ህብረተሰቡ በአረም ማፅዳት ዘመቻው በሚከናወኑ ተግባራት አስፈላጊውን ግንዛቤ ከመድረኩ ማግኘቱን ተናግረዋል ። በዘመቻው ንቃት በመሳተፍ የድርሻቸውን  ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል። የሐዋሳ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን በመወከል መድረኩ ላይ የተሳተፋት ወይዘሮ መዓዛ መንግስቱ በበኩላቸው አረሙን ከሐይቁ ለማጽዳት የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎች እንዲቀርቡ መስሪያ ቤታቸው የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል። አባያ ሐይቅ ያጋጠመውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በሰው ኃይል አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ የገለጹት ደግሞ ስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋስስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ከበደ ካንቹላ ናቸው፡፡ በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ስርጸት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ተሾመ ይርጉ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሐይቁን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ዋነኛው አጋር በመሆን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደምሰጥ አስታውቀዋል። የደቡብ ክልል አከባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን ዋና ዳይረክተር አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ አባያ ሐይቅ ከእምቦጭ አረም ለመታደግ የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር የተዘጋጀው መድረክ የታለመለትን ዓላማ ለማሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ በመድረኩ የተሳተፋ ባለድርሻ አካላት በዘመቻው ሊያከናውኑ የተከፋፈሉትን የስራ ድርሻ በአግባቡ በመፈፀም ሐይቁን ከአደጋ የማዳን ተልዕኳቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የክልሉ አከባቢ ጥበቃና ደን ልማት እና እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮዎች ዘመቻውን እንዲያስተባብር የተቋቋመውን ግብረ ኃይል እንዲመሩ ተመርጠዋል ። እንዲሁም የክልሉ ኮሙዪኒኬሽን ጉዳዮች፣ ባህልና ቱርዝም ቢሮዎችና መገናኛ ብዙሃን ድርጅት እንዲሁም የብዝሃ ህይወትና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአባልነት ተካተዋል። በዞንና በወረዳ ደረጃም ተመሳሳይ ግብረ ኃይል የተደራጀ ሲሆን በዚህም ኃላፊነትና ተግባር አስመልክቶ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ በመወያየት  ፀድቋል ። ዘመቻው የሚካሄደው ከግንቦት 15/2010ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር እንደሆነም በመድረኩ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም