የጌዴኦ ዞን በሕገ ወጥ ንግድ በተሳተፉ 63 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ወሰደ

120

ዲላ ፤ ህዳር 7/2015 (ኢዜአ) በህገወጥ ንግድ ተሳትፈው የተገኙ 63 የንግድ ድርጅቶች እርምጃ እንደተወሰደባቸው የጌዴኦ ዞን የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው "የንግድ ስርዓቱን ፍትሃዊ ለማድረግ የሽማቹን መብት ለማስጠበቅ የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ ነው" በሚል ሀሳብ  መምሪያ ያዘጋጀው የውይይት መድረከ  በዲላ ከተማ ተካሄዷል።

በዞኑ ባለፉት አራት ወራት ህገወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር በተካሄደው እንቅስቃሴ 63 የንግድ ድርጅቶች ባለቤቶች በፈጸሙት ጥሰት በህግ እንዲጠየቁ መደረጉን የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ ምስጋና በራሶ በመድረኩ ተናግረዋል።

ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ፣ ባዕድ ነገር ቀላቅሎ መሸጥ ፣  ምርት መደበቅና ማሸሽ  የንግድ ድርጅቶቹ ከፈጸሙት ህገ ወጥ ተግባር መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በዚህም ለህግ ቀርበው በተመሰረተባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው እስራትና ንብረታቸውን በቁጥጥር ስራ በማዋል  ከንግዱ ስርዓት ውጭ እንዲሆኑ የማድረግ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

የንግድ ስርዓቱን ፍትሃዊ ለማድረግና የሽማቹን መብት ለማስጠበቅ የዋጋ ጭማሪ ቁጥጥርን ጨምሮ ሌሎችን ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎቸን ለመከላከል ግብረሃይል ተቋቁሞ በተደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን ኃላፊዋ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ሻጭና ሽማቾችን በቀጥታ ለማገናኘትም በዲላ ከተማ የተጀመረውን የእረፍት ቀናት ገበያ በሁሉም አካባቢዎች አስፋፍቶ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የዲላ ከተማ ንግድ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሻለቃ አረጋኸኝ አሰፋ በበኩላቸው እንዳሉት በአካባቢው በሚመረቱ የቡና፣ የእንሰት ተዋጽኦና የቁም እንስሳት ግብይት ላይ የደላሎች መብዛት  በፈጠረው ረጅም ሰንሰለት ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሆኗል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ፤ የእንስሳት ግብይት ማዕከላትን በማጠናከር ህገወጥ ደላላን ለማስቀረት አስተዳደሩ ከፀጥታ መዋቀር ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በዚህም ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።

ያለደረሰኝ የሚደረግ ግብይትና ህገወጥ ዋጋ ጭማሪ እንዲሁም የአገልግሎት ጊዜ ያለፈ ዕቃዎችና መድኃኒቶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ውጤት እንዲያመጣ ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሊያግዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም