በስካይ ኒውስ አረብኛ እና አማርኛ ቻናሎች የኢትዮጵያን እውነታ ለአለም ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት እናደንቃለን-አቶ መሃመድ እድሪስ

128

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 7 ቀን 2015 በአይ ኤም አይ ግሩፕ ስር ባሉት በስካይ ኒውስ አረብኛና አማርኛ ቻናሎች የኢትዮጵያን እውነታ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም ለአረቡ አለም ለማድረስ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያደንቁ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ ገለጹ።

ዋና ዳይሬክሩ በአረብ ኢምሬትስ አቡዳቢ እየተካሄደ ባለው አለም አቀፍ የሚዲያ ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

አቶ መሀመድ እድሪስ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከኢንተርናሽናል ሚዲያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ (ኤይ ኤም አይ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ናርት ብራውን ጋር በኢትዮጵያ ያለውን እድል በመጠቀም በሚዲያው ዘርፍ የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ግንኙነትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ውይይታቸውን አስመልክቶ ለአል ዐይን ኒውስ ዋና አዘጋጅ ሰኢድ አል አላዊ እንደገለጹት በአይ ኤም አይ ግሩፕ ስር ባሉት በስካይ ኒውስ አረብኛ እና አማርኛ የኢትዮጵያን እውነታ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በዋናነትም ለአረቡ አለም ለማድረስ የሚያደርጉትን ጥረት ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ ለዋና ስራ አስፈጻሚው ናርት ብራውን አስረድተዋል።

አል አይን አማርኛ እና አረብኛ ቋንቋ በቀጣይም የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገፅታ ለአለም ተደራሽ እንዲያደርግ የሚያስችል ምክክር ማድረጋቸውን ያነሱት አቶ መሀመድ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ግሩፑ በኢትዮጵያ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንን በስልጠናና በአቅም ግንባታ እንዲያግዝ መጠየቃቸውንና አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸው በቀጣይም በኢትዮጵያ ያለውን ተደራሽነት እንዲያሰፋ መጋበዛቸውንም አስረድተዋል።

የኤይ ኤም አይ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናርት ብራውንም በኢትዮጵያ ያለውን የሚዲያ ስራ አጠናከረው እንደሚቀጥሉ ተናረዋል፡፡

ግሩፑ በቀጣይም በሚዲያ ዘርፍ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው ወደ ኢትዮጵያም እንደሚመጡ ቃል መግባታቸውን አቶ መሃመድ ተናግረዋል።

የአል ዐይን ኒውስ ዋና አዘጋጅ ሰኢድ አል አላዊም ከዋና ዳይሬክተሩ ጋር በመገናኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በበኩላቸው የኢትዮጵያን ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉን በሙያቸው ለማገዝ እንደሚፈልጉም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም