በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ይሁንታ ከሰጣቸው 34 እጩዎች 31ዱ አሸንፈዋል - ‘የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’

77

ሕዳር 7 /2015 በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ይሁንታ ከሰጣቸው 34 እጩዎች 31ዱ ማሸነፋቸውን ‘የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’(ኤፓክ) የተሰኘው የፖለቲካ ተግባር ኮሚቴ አስታወቀ።

ባሸነፉት እጩዎች በአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች አዲስ የኢትዮጵያ ደጋፊ ስብስብን (ኮከስ) ለመመስረት መታሰቡን አመልክቷል።

23ኛው የአሜሪካ አጋማሽ ዘመን ምርጫ ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን ከጥቂት ቦታዎች በስተቀር በአብዛኛው አካባቢዎች የምርጫ ውጤት ይፋ ሆኗል።

‘የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ በምርጫው በኮንግረስና ሴኔት፣በግዛት አስተዳዳሪና በሌሎች አካባቢያዊ ምርጫዎች ለተሳተፉ 34 እጩዎች እውቅና መስጠቱ ይታወቃል።

ኤፓክ ከተቋቋመበት አላማ አንዱ የሆነውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንዲሁም በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ መስራት እንደሆነና እጩዎች ይሄን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ድጋፍ ማግኘታቸውን አመልክቷል።

ይሁንታ ከተሰጣቸው እጩዎች መካከል 31ዱ እውቅና ማግኘታቸውን የኤፓክ ሊቀመንበር አቶ መስፍን ተገኑ ገልጸዋል። የሁለት እጩዎች የምርጫ ውጤት እየተጠበቀ ነው ብለዋል።

ቲም ኪን (ኒው ጀርዚ ሪፐብሊካን ፓርቲ)፣አቢጌል ስፓንበርገር (ቨርጂኒያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፣ሲድኒ ካምላገር (ካሊፎርኒያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፣ሼይላ ጃክሰን ሊ (ኒው ዮርክ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፣ ብራያን ፊትዝፓትሪክ (ፔንሲልቫኒያ ሪፐብሊካን ፓርቲ)፣ ጆን ጋራሜንዲ (ካሊፎርኒያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፣ አል ግሪን (ቴክሳስ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፣ ስቴቨን ሆርስፎርድ (ኔቫዳ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፤ ትሬንት ኬሊ (ሚሲሲፒ ሪፐብሊካን ፓርቲ)፣ ጂሚ ፓኔታ (ካሊፎርኒያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ)፣ ጋይ ሬስቼንትሀለር (ፔንሲልቫኒያ ሪፐብሊካን ፓርቲ)፣ ዴቪድ ሽዋይከርት (አሪዞና ሪፐብሊካን ፓርቲ) እና ክሪስ ስሚዝ (ኒው ጀርዚ ሪፐብሊካን ፓርቲ) የኮንግረስ መቀመጫን ካሸነፉት መካከል ናቸው ።

ጆን ፌተርማን (ፔንሲልቫኒያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ) እና ጀምስ ዴቪድ ቫንስ( ኦሃዮ ሪፐብሊካን ፓርቲ) የሴኔት መቀመጫ ካሸነፉ እጩዎች መካከል ይገኙበታል።

በኒው ጀርዚ ግዛት ዌስት ኦሬንጅ ካውንቲ (አውራጃ) በማዘጋጃ ቤታዊ ምርጫ(City Council) የተወዳደረችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አስመረት ገብረሚካኤል ማሸነፏ ይታወቃል።

የኤፓክ ሊቀመንበር አቶ መስፍን ተገኑ የተገኘው ውጤት ለኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት ታሪካዊ የሚባል አንደሆነ ገልጸዋል።

ባሸነፉት እጩዎች እ.አ.አ በ2023 በአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች የኢትዮጵያ ደጋፊ ስብስብን (ኮከስ) ለመፍጠር መታሰቡን ተናግረዋል።

በአባላቱ በሴኔትና ኮንግረሱ የኢትዮጵያ ጥቅም የሚያስከብሩ እንዲሁም የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጎለብቱ ረቂቅ ሕጎች ተዘጋጅተው እንዲጸድቁ ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።

ኮሚቴው በቀጣይ ተቋማዊ አቅሙን ማጠናከር፣ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ መስፍን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም