የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ለከተማ ግብርና የሚውሉ 200 የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰጠ

96

አዲስ አባባ /ኢዜአ /ህዳር 7/2015 የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ለከተማ ግብርና የሚውሉ 200 የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ አደረገ፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሚኒስትር አይሻ መሐመድ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ ድጋፉ በአዲስ አበባ በተቋማት እና በግል ይዞታ የሚገኙ መሬቶች ላይ የተጀመረውን የከተማ ግብርና ውጤታማነት ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በመዲናዋ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የከተማ ማስዋብ ስራን ለማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት።

ድጋፉን የተረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው  ህዝቡን በማስተባበር በመዲናዋ የከተማ ግብርናን ጨምሮ የህብረተሰቡን ኑሮ የሚቀይሩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ለዚህም ስኬት የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን በማንሳት።

በድጋፍ የተሰጡትን የውሃ መሳቢያ ፓምፖችም  በመዲናዋ ለሚመለከታቸው አካላት በማሰራጨት በከተማ ግብርና ዘርፍ ውጤታማ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

በተለይም  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለውን ስራ ስኬታማ ለማድረግ ድጋፉ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም