የኦሮሚያ ክልል የመስኖ ስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ ግብዓቶችና የግብርና መሳሪያዎች እያቀረበ ነው

245

ጅማ (ኢዜአ) ህዳር 07 ቀን 2015  የኦሮሚያ ክልል የመስኖ ስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ ግብዓቶችና የግብርና መሳሪያዎች እያቀረበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድሳኒ አሚን በክልሉ በስንዴ ልማት ውጤታማ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በዚህም የጅማ ዞንን ጨምሮ ለተለያዩ ዞኖች 4 ሺህ ትራክተሮችና 39 ሺህ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ለማህበራትና ለአርሶ አደሮች ተሰራጭተው የመስኖ ልማት ስራው እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ በሜካናይዜሽን የታገዘ የመስኖ ስንዴ የመዝራት ስራ እየተሰራ ሲሆን ዛሬ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የስራ ሃላፊዎችም በዞኑ መንቾ ወረዳ በዘመቻ  እየተከናወነ  ያለውን  የመዝራት ስራ ጎብኝተል።

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው ዞኑ በበጋ የመስኖ ስንዴ የተሻለ ምርት ለማግኘት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ዘንድሮ 200 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የመስኖ ስንዴ ለመዝራት መታቀዱን የገለጹት አስተዳዳሪው ከዚህም እስከ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።

አስካሁንም በዞኑ 50 ሺህ ሄክታር መሬት የተዘራ ሲሆን 150 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ ለዘር ዝግጁ ሆኗል ነው ያሉት።

''በዛሬው እለትም የመንቾ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች 5 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ተሸፍኗል'' ብለዋል።

በመስኖ ስንዴው ልማት 290 ሺህ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን የተደራጁ 50 ሺህ ወጣቶችም በዘርፉ የስራ እድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በልማቱ ተሳታፊ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል አባጀሃድ አባጊሳ እንዳሉት ''የጊቤን ወንዝ ተጠቅመን ስንዴን በኩታ ገጠም እየዘራን ነው፤ በምርቱ ተጠቃሚ እንደምንሆንም ተስፋ አለን'' ብለዋል።  

ከዚህ በፊት የመስኖ ስንዴ ልምዱ እንደሌላቸው የገለጹት አርሶ አደር ፋጂ ሰማን በበኩላቸው ዘንድሮ መንግስት ባደረገላቸው የምርጥ ዘርና የውሃ መሳቢያ ሞተር እገዛ ተነሳስተው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም